የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአምስት ሚኒስትሮችን ሹመት አጸደቀ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2017(ኢዜአ)፦የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀረቡለትን የአምስት ሚኒስትሮችን ሹመት በአንድ ተቃውሞ፣ በሁለት ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።


 

ሹመታቸው የፀደቀው የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የፍትህ ሚኒስትር ሃና አርአያሥላሴ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ናቸው።

በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፥ ሹመቱ ብቃታቸውን በተግባር ያስመሰከሩ ወጣቶችና ሴቶችን ያካተተ መሆኑን ገልጸው፥ አገልጋይ አመራር መገንባት ላይ የተሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የሚኒስትሮች ሹመት አካታችና የፆታ ስብጥርን ያማከለ መሆኑም ተጠቅሷል።

ሚኒስትሮቹ በስራ ልምዳቸውና በትምህርት ዝግጅታቸው ለተሾሙበት መንግሥታዊ ኃላፊነት ብቁ መሆናቸውን አብራርተዋል።


 

መንግስት እንደ አገር የተጀመሩትን የተቋማት ሪፎርም ስራዎች በብቃትና በውጤታማነት የሚመሩ ሚኒስትሮችን ለሹመት ማቅረቡንም ገልፀዋል።

የምክር ቤቱ አባላት የሚኒስትሮቹ ሹመት ላይ ውይይት ካደረጉ በኋላ ሹመቱን በአንድ ተቃውሞ፣ በሁለት ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቀዋል።

ተሿሚ ሚኒስትሮችም በምክር ቤቱ ተገኝተው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም