ጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥ ቀውሶችን ለመከላከልና ለመቋቋም የሚበጁ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት በመሆኑ ኢትዮጵያ በቂ ዝግጅት አድርጋለች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2017(ኢዜአ)፦ በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ-29) የአየር ንብረት ለውጥ ቀውሶችን ለመከላከልና ለመቋቋም የሚበጁ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት በመሆኑ ኢትዮጵያ በቂ ዝግጅት ማድረጓን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ገለጹ።

በእንግሊዝኛው (Conference of Parties -COP) የሚሰኘው የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ዓመታዊ ጉባዔ የፊታችን ሕዳር ወር መባቻ ጀምሮ በአዘርባጃን ባኩ ከተማ ይካሄዳል።

ጉባኤው ዓለምን ክፉኛ እየፈተነ በሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ መፍትሄ ለማበጀት የሀገራት መሪዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት፣ የሚደራደሩበትና የጋራ ውሳኔ የሚተላለፍበት መድረክ ነው።

አቶ ሥዩም መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ-29) የአየር ንብረት ለውጥ ቀውሶችን ለመከላከልና ለመቋቋም የሚበጁ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት በመሆኑ ኢትዮጵያ በቂ ዝግጅት አድርጋለች።

ኢትዮጵያ ችግሩን ለመቋቋም በራሷ አቅም የነደፈቻቸውን ኢኒሼቲቮች ገቢራዊ በማድረግ ተምሳሌታዊ ስራዎችን እያከናወነች መሆኑን አረንጓዴ አሻራ፣ ሌማት ትሩፋትና ጽዱ ኢትዮጵያን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በዋናው ጉባኤ እና በተጓዳኝ ስብሰባዎች በንቃት በመሳተፍም ተሞክሮዋን ለዓለም ለማጋራት እና ከሌሎች ልምድ ለመለዋወጥ መድረኩን በአግባቡ እንደምትጠቀምበት ተናግረዋል።

በተለይም የጀመረቻቸውን ኢኒሼቲቮች ከግብ ለማድረስ የፋይናንስ ፍሰት አቅም በመገንባት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን የሚቋቋም ሀገርና ማህበረሰብ ለመገንባት በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

ባለፈው ዓመት በዱባዩ ኮፕ-28 የተፈጠሩ የትብብርና አጋርነት ስራዎች በትግበራ ሂደት ላይ መሆናቸውንም አስታውሰዋል።

በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ) ላይ የሚተላለፉ ውሳኔዎች ተፈጻሚነት አናሳ በመሆኑ ተፅዕኖዎች እየተባባሱ መምጣታቸውን የገለጹት ደግሞ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ናቸው።

በሥነ ሕዝብ፣ ጤና እና አካባቢ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ 99 ሲቪል ማህበራትን ያቀፈው ፒ.ኤች.ኢ.ኢ.ሲ የተሰኘው ጥምረት በአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤዎች ላይ የካበተ ልምድ አለው።

የጥምረቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳሻው ሞገሴ እንደሚሉት፤ ጥምረቱ ከተመሰረተ ጀምሮ ላለፉት 17 ዓመታት በሥነ ህዝብ፣ በጤናና በአካባቢ ጉዳዮች የተቀናጀና ዘላቂ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል።


 

የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ(ኮፕ) በ30 ዓመታት ቆይታው የተላለፉ ውሳኔዎች ተፈጻሚነት አናሳ ነው ይላሉ።

ውሳኔዎቹ በተፈራራሚ ሀገራት በቅጡ ባለመተግበራቸው ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውሶች እየተባባሱና የሚያሳድሯቸው ተጽዕኖዎችም እየሰፉ መምጣታቸውን ነው ያነሱት።

ለአብነትም የችግሩ ዋና መንስኤ የሆኑ የበለጸጉ ሀገራት በየዓመቱ 100 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ እንዲከፍሉ የተደረሰው የፓሪስ ስምምነት በተሟላ ሁኔታ እንዳልተተገበረ ጠቅሰዋል።

ያም ሆኖ የጉባኤው መካሄድ ተጨማሪ ጫና ለማሳደር፣ ለአጋርነት ምስረታ እና የፋይናንስ ድጋፍ ለማሰባሰብ ይበጃል ባይ ናቸው።

የሥርዓተ ምህዳር ፍትህ ኢትዮጵያ ሀገር በቀል ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት መስራችና ዋና ዳይሬክተር እስከዳር አውግቸው በበኩላቸው፤ የአየር ንብረት ለውጥና አካባቢ ጥበቃ ፍትህ ይሻል ይላሉ።


 

በሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት በአካባቢ ላይ በሚደርሰው ተፅዕኖ ኢትዮጵያን ጨምሮ ታዳጊ ሀገራት የገፈቱ ቀማሽ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ በጉባኤው የጉዳት ካሳና መቋቋምን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበት ያነሳሉ።

ሲቪል ማህበራት በኮፕ ድርድር ሀገራትን ወክለው ባይሳተፉም ከአቻ ማህበራት ጋር በመቀናጀት ለሰው ልጆች ሁሉ የሚጠቅሙ ውሳኔዎች እንዲወጡ የማስረዳትና የድርድር ሃሳቦችን የመሸጥ ሚና ይወጣሉ ነው ያሉት።

ከዓመታዊ ስብሰባ ባሻገር ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ ውሳኔዎች እና እርምጃዎች እንዲወሰዱ ተደራዳሪ ሀገራትም የገቧቸውን ቃሎች መተግበር ይገባቸዋል ባይ ናቸው።

የሲቪል ማህበረብ ድርጅት የስራ ኃላፊዎቹ ዘንድሮ በአዘርባጃን በሚደረገው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በእስካሁን ድርድሮች በእንጥልጥል ላይ የቆዩ ረቂቅ የስምምነት ሰነዶች ይጸድቃሉ ብለው ተስፋ አድርገዋል።

በተለይም የዘንድሮው ጉባኤ ትኩረት የፋይናንስ ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ፤ የተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነቶች እንደሚደረጉ ይጠበቃል ነው ያሉት።

የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድራቸው ተፅዕኖዎች እየሰፉ መምጣት በተለይም በአፍሪካ ያሳደሩትን ጫና የመቋቋምና የጉዳት ካሳ(ሎስ ኤንድ ዳሜጅ) ስምምነቶች እንደሚተላለፉ በተስፋ እንጠብቃለን ብለዋል።

ከተጎጂ ማህበረሰቦች፣ ከስርዓተ ጾታ እና ከአካታች የአየር ንብረት ለውጥ አንጻርም እርምጃዎችና ማዕቀፎች እንዲወጡም እንዲሁ።

በዘንድሮው የኮፕ ስብሰባ በቅድመ ሁነቶችና በሁነቶች ላይ ከዓለምአቀፍ አቻ ድርጅቶች ጋር ትስስርና አጋርነት በመፍጠር ለዓለም የሚበጁ ውሳኔዎች እንዲወጡ በንቃት እንደሚሳተፉ ኃላፊዎቹ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም