ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የስድስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የስድስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።

ኢትዮጵያ መድን ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ  የሚመራው ኢትዮጵያ መድን በሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲሸነፍ በሶስቱ አቻ ወጥቷል።

በጨዋታዎቹ ምንም ግብ ያላስቆጠረው ኢትዮጵያ መድን አንድ ግብ አስተናግዷል። ቡድኑ በሶስት ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ኢትዮጵያ መድን በውድድር ዓመቱ ምንም ግብ ያላስቆጠረ ብቸኛው የሊጉ ክለብ ነው።

ተጋጣሚው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ እስከ አሁን በሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሽንፈትን አስተናግዷል። ቡድኑ አንድ ግብ ብቻ ሲያስቆጥር 7 ጎሎችን አስተናግዷል።

በአሸናፊ በቀለ የሚሰለጥነው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን 18ኛ ደረጃ ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

በሌላኛው የስድስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ፋሲል ከነማ ከአርባምንጭ ከተማ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ፋሲል ከነማ በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች አንዱን ሲያሸንፍ አራት ጊዜ አቻ ወጥቷል።

በአምስቱ ጨዋታዎች ቡድኑ አምስት ጎሎችን ሲያገባ አራት ግቦች ተቆጥረውበታል።

በውበቱ አባተ የሚሰለጥነው ፋሲል ከነማ በሰባት ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

ተጋጣሚው አርባምንጭ ከተማ እስከ አሁን በሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ሁለት ጊዜ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

በአራቱ ጨዋታዎች ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥር አምስት ግቦችን አስተናግዷል።

በበረከት ደሙ የሚመራው አርባምንጭ ከተማ በአራት ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

የሊጉ መርሃ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል ባህር ዳር ከተማ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 10 ሰዓት፣ ሀዲያ ሆሳዕና ከወላይታ ድቻ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ስሑል ሽሬ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የሳምንቱ አራፊ ቡድኖች ናቸው።

ሲዳማ ቡና ሊጉን በ12 ነጥብ እየመራ ይገኛል።

የመቀሌ 70 እንደርታው ያሬድ ብርሃኑ በአምስት ግቦች የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየመራ ይገኛል።

የወላይታ ድቻው ያሬድ ዳርዛ እና ዩጋንዳዊው የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች ቻርልስ ሙሲጌ በተመሳሳይ አራት ግቦች ይከተላሉ።

የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆዩ የሊጉ አክሲዮን ማህበር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም