ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ እና በማሌዢያ በነበራቸው ጉብኝት ስኬታማ ቆይታ አድርገዋል- ቢልለኔ ስዩም - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ እና በማሌዢያ በነበራቸው ጉብኝት ስኬታማ ቆይታ አድርገዋል- ቢልለኔ ስዩም
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2017(ኢዜአ)፦ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ እና በማሌዢያ በነበራቸው ይፋዊ የስራ ጉብኝት ስኬታማ ቆይታ ማድረጋቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።
16ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ በሩሲያ ካዛን መካሄዱ ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሚኒስትሮች ልዑካን ቡድን ጋር በመሆን በጉባዔው ላይ ተሳትፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሚኒስትሮች ልዑካን ቡድን ጋር በመሆን በማሌዢያ ኳላላምፑር ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸውም ይታወቃል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ እና በማሌዢያ የነበራቸውን የስራ ጉብኝት አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ኢትዮጵያ አባል ከሆነች በኋላ የተሳተፈችበት የመጀመሪያው ጉባዔ መሆኑን ኃላፊዋ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባዔው ላይ፣ በሁለትዮሽ እና በባለብዝሃ ወገን የምክክር መድረኮች ላይ ውጤታማ ተሳትፎ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባዔው ላይ አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ማግኘት እንዳለባት እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓቱ እንዲሻሻል ጥሪ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
የፀጥታው ምክር ቤት እና የፋይናንስ ስርዓት ማሻሻያው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ደጋግመው ሲያነሷቸው የቆዩ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) ከጉባዔው ጎን ለጎን ከብሪክስ አባል እና አባል ለመሆን ከሚፈልጉ አገራት መሪዎች ጋር በተደረጉ የሁለትዮሽ ውይይቶች በማድረግ የኢትዮጵያን አቋሞች ማንጸባረቃቸውን አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማሌዢያ በነበራቸው ይፋዊ የስራ ጉብኝት ከአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም ጋር መወያየታቸውን የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊዋ ገልጸዋል።
በውይይቱ ወቅት የሁለቱን ሀገራት ለረጅም ጊዜ የቆየ ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማሌዢያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ አየር ተጠቅመው በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ ማቅረባቸውን አመልክተዋል።
“Tiger Economies” የሚል ስያሜ ከተሰጣቸው አገራት መካከል አንዷ ከሆነችው ማሌዢያ ኢትዮጵያ ልምድ መቅሰም እንደምትሻም በውይይቱ ወቅት መነሳቱን ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከውይይታቸው ጎን ለጎን የፕሮቶን የመኪና መገጣጠሚያ ማዕከል እና ከተማን የማዘመን ስራዎችን ጨምሮ የተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎችን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ እና በማሌዢያ በነበራቸው ጉብኝት ስኬታማ ቆይታ ማድረጋቸውን ኃላፊዋ አመልክተዋል።