ቀጥታ፡

የዓለም እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የአፍሪካ ሻምፒዮና በአዲስ አበባ ይካሄዳል 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2017(ኢዜአ)፦  የዓለም እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ዋንጫ አህጉራዊ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና (IHF Trophy Africa) ከጥቅምት 23 እስከ 27 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይደረጋል።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ከዓለም አቀፍ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን እና ከአፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ሻምፒዮናውን እንደሚያካሂድ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በሚደረገው ሻምፒዮና  ኢትዮጵያ፣ ጊኒ፣ ማዳጋስካር፣ ካሜሮን፣ ናይጄሪያ እና ዛምቢያ በወጣቶች ከ18 ዓመት በታች ይወዳደራሉ።



ኮንጎ ሪፐብሊክ ፣ጋና፣ ጊኒ፣ ሩዋንዳ እና ዚምባብዌ ከ20 አመት በታች የሚወዳደሩ አገራት ናቸው።

የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በሻምፒዮናው ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በመገኘት አበረታተዋል።

የአፍሪካ ሻምፒዮናን አልፋችሁ ለዓለም አቀፍ ውድድር እንደምትደርሱ እምነት አለኝ፤ በርትታችሁ ስሩ የአሸናፊነት መንፈስን መጎናጸፍ አስፈላጊ ነው ብለዋል ሚኒስትሯ ።

መንግስት ለብሔራዊ ቡድኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፍትህ ወልደሰንበት (ዶ/ር)  እና የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ዋና ኢንስፔክተር ተስፋዬ ሙለታ በተደረገላቸው ማበረታታት በጣም ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው መንግስት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።


የዓለም እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ዋንጫ አህጉራዊ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና አንደኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ ሃገራት  አፍሪካን በመወከል የዓለም እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ሻምፒዮና ላይ ይሳተፋሉ።

ሻምፒዮናው በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ እህትማማች ሀገሮች መካከል የመቀራረብ፤ የመተዋወቅ እና የመደጋግፍን ባህል ለማዳበር እንደሚያግዝ ከባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም