ቀጥታ፡

በአቶ አደም ፋራህ የተመራው ልዑካን ቡድን ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የኦርጋናይዜሽን ዲፓርትመንት ጋር የልምድ ልውውጥ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2017(ኢዜአ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ እና በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የተመራ ልዑክ ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የኦርጋናይዜሽን ዲፓርትመንት ጋር የልምድ ልውውጥ አካሂዷል፡፡

አቶ አደም ፋራህ በልምድ ልውውጡ ብልጽግና አዲስ ፓርቲ ቢሆንም በመላ ሀገሪቱ መዋቅር ዘርግቶ የተደራጀ ስራ ለመስራትና የአባላቱን እቅም ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዚህም መልካም ውጤት ማስመዝገቡን የገለፁት፣ አቶ አደም በቀጣይ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከመቶ አመት በላይ ልምድ ካለው ፓርቲ ተሞክሮ ለመቅሰም ዝግጁ መሆኑን አንስተዋል።

የሲፒሲ ኦርጋናይዜሽን ዲፓርትመንት ምክትል ሚኒስቴር ሺ ቺፋንግ በበኩላቸው የሲፒሲ የኦርጋናይዜሽን አሰራር ስርዓት፣ የአሰራር ስርአት እና አጠቃላይ ሁኔታውን በሚመለከት ተሞክሮዎችን አጋርተዋል፡፡

ዲፓርትመንቱ ወደ ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጉ የሲፒሲ አባላትን ከላይ እስከ ታች ለማደራጀት፣ አቅማቸውን ለማልማት እና በቀጣይነት አቅማቸውን ለመገንባት እያደረጋቸው ያሉ ዋና ዋና ስራዎች እንዲሁም እያገኛቸው ያሉ ውጤቶች እና በቀጣይም እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ከላይኛው የፓርቲ መዋቅር እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ያለውን ለመዘርጋት ሀሳብና አቋም የሚሰሩ ስራዎችን አጋርተዋል፡፡


 

የልዑኩ መሪ አቶ አደም ፋራህ ብልጽግና ፓርቲ ከአደረጃጀት አንፃር  እያከናወናቸው ያሉ ዋና ዋና ጉዳዮችን አጋርተዋል፡፡

በተጨማሪም በቀጣይነት በዚህ ዘርፍ ይበልጥ ትብብር ለማሳደግ በተለይም የአቅም ግንባታና የአባላት ልማት፣ የፓርቲ መዋቅርን ማጠናከር እንዲሁም "በዲጂታል ፓርቲ" ግንባታ መስክ ቴክኖሎጂን አልቆ መጠቀም የሚችል ፓርቲ አንዴት መገንባት ይቻላል በሚሉ ዙሪያ ላይ አብረው ለመስራት እና የበለጠ እየተደጋገፉ ለመቀጠል ጥሪ አቅርበዋል።

የሲፒሲ የዲፓርትመቱ ሃላፊም በእነዚህ ጉዳዮች ድጋፍ ለማድረግና ትብብራቸውን ለማጠናከር ዝግጁነታቸውን መግለፃቸውን ከፓርቲው ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም