በርካታ አቅመ ደካሞች እፎይታ ያገኙበት የጤና አገልግሎት

በሀገር ደረጃ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር አሁን ላይ  56 ሚሊዮን ደርሷል፤  ዓላማውም ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትንና ጥራትን ማረጋገጥ ነው። ይህ አገልገሎት የማህብረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ይሰኛል።

አገልግሎቱ ዜጎች አስቀድመው በሚከፍሉት አነስተኛ መዋጮ የጤና እክል በሚያጋጥማቸው ወቅት ያለምንም የክፍያ ስጋት የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ  ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት አጠቃቀምን ለማጎልበት ያለመ ስርዓት ነው።

በአዲስ አበባ ከ2010 ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ የጀመረ ሲሆን በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ  እንደቻለ ኢዜአ ካነጋገራቸው ተጠቃሚዎች ሰምቷል።


 

አቶ ብዙአየሁ ሲሳይ ልደታ አካባቢ በሚገኘው በለጡሽ ጤና ጣቢያ አባልነታቸው ለማሳደስና ልጆቻቸውን ሊያሳክሙ መጥተው ነው ያገኘናቸው። 

የጤና መድህን አባል ከሆኑ ሁለት ዓመታት እንደሆናቸው የነገሩን አቶ ብዙአየሁ፥ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸው የቤተሰባቸውን ጤንነት ለመጠበቅ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል።

የቤተሰባቸው አባል ህመም ሲያጋጥመው በመምጣትም በዓመት አንድ ጊዜ በምፈጽመው የጤና መድህን  አባልነት ክፍያ አስፈላጊውን አገልግሎት እያገኘሁ ነው ይላሉ።


 

በጡረታ በሚያገኟት ገንዘብ የሚተዳደሩት አቶ በቀለ ጉተማ በበኩላቸው፥ ከእድሜ ጋር ተያይዞ እሳቸውና ባለቤታቸው የስኳርና ደም ግፊት ህክምና እየተከታተሉ መሆናቸውን ይናገራሉ።

በጡረታ ገንዘብ የኑሮ ወጪን ሸፍኖ የህክምና ክትትል ማድረግና መድሀኒት መግዛት እንደሚከብድ ያነሱት አቶ በቀለ፤ ሆኖም የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸው የህክምና ወጪ ሳያሳስባቸው ተገቢ አገልገሎት እያገኙ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

መንግስት በጤና መድህን አገልግሎት ዜጎች ህክምና እንዲያገኙ ማድረጉ በተለይ በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ዜጎችና ለአቅመደካሞች ፋይዳው ቀላል አይደለም ነው ያሉት። 

እንደእኔ እርጅና ተጭኖት ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን ይዞ ኑሮውን ለሚገፋ ሰው የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ፍቱን ነው የሚሉት ደግሞ ወይዘሮ ገነት አለማየሁ ናቸው።


 

በዓመት አንዴ በሚደረግ ክፍያ ዓመቱን ሙሉ ህክምና ማግኘት መቻል ለብዙኃኑ ሸክም አቅላይ አገልግሎት ነው ያሉት ወይዘሮ ገነት፥ አባልነታቸውን በየዓመቱ እያሳደሱ እየተጠቀሙ መሆኑንም ያነሳሉ።

የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች የጤና መድህን አባል በመሆናቸው ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ተገቢውን የህክምና እና የመድሃኒት አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ነው የተናገሩት።

አስተያየት ሰጪዎቹ በጤና መድህን አገልግሎት አልፎ አልፎ የሚስተዋለውን የመድሃኒት አቅርቦት እጥረት በቀጣይ የተሻለ ለማድረግ እንዲሰራ ጠቁመዋል። 

የጤና መድህን አባል ያልሆኑ የመዲናዋ ነዋሪዎችም  ህመም በሚያጋጥምበት ወቅት ንብረት ከመሸጥ እስክ ብድር ዕዳ ከመግባት በቀላል ዓመታዊ ወጪ ለመታከም የጤና መድህን አባል እንዲሆኑ ምክራቸውን ለግሰዋል።


 

የአዲስ አበባ ጤና መድህን ክላስተር ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አይካ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ዋነኛ ዓላማ ማህበረሰቡ ዝቅተኛ የሆነ ዓመታዊ ወጪ በማዋጣት ህመም በሚያጋጥማቸው ወቅት ለክፍያ ሳይጨነቁ አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል ነው ብለዋል። 

በዚህም በመዲናዋ በርካታ ነዋሪዎች በዝቅተኛ ወጪ የጤና አገልግሎቶችን እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የመድሃኒት እጥረት እንዳይከሰትም ከከነማ ፋርማሲና ከሌሎች መድሃኒት አቅራቢ ተቋማት ጋር ስምምነት በመፈራረም እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

እንዲሁም በሆስፒታሎች ባሉ የማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲዎች መድሃኒት ለታካሚዎች እየቀረበ ነው ብለዋል። 

በከተማ አስተዳደሩ ከጥቅምት 1 ጀምሮ እስከ ህዳር 30 ቀን 2017 ድረስ የሚቆይ የጤና መድህን አገልግሎት የአባልነት ምዝገባ እና እድሳት እየተከናወነ በመሆኑ ህብረተሰቡ እንዲመዘገብ ጥሪ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም