ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ የከርሰ-ምድር ውሃ ሃብቷን በአግባቡ ለመለየትና ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራች ነው-የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 18/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ የከርሰ-ምድር ውሃ ሃብቷን በአግባቡ ለመለየትና በፍትሐዊነት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ዝርዝር ጥናት እንደሚደረግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ቁጥርና የልማት ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ ከገፀ-ምድር ውሃ በተጨማሪ የከርሰ-ምደር ውሃን መጠቀም ወሳኝ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፣ የውሃ ሀብትን በአግባቡ መምራትና ማስተዳደር በዘላቂነት ለመጠቀም ያስችላል።

ኢትዮጵያ የከርሰ ምድርና የገጸ-ምድር ውሃ ሃብቷ በትክክል ጥቅም ላይ እንዲውል የውሃ ምንጮቹን በአግባቡ መለየትና መጠበቅ እንዳለባት በውሃ ሀብት ፖሊሲ ላይ በዝርዝር መቃኘቱን ገልጸዋል።

እየጨመረ የመጣው የህዝብ ቁጥር፣ የአየር ንብረት ለውጥና የከተሞች መስፋፋት በገጸ-ምድር ውሃ ላይ ጫና ሊያሳድሩ እንደሚችሉም ነው ያነሱት።

ይህን ጫና ለመቀነስ ከገጸ-ምድር ውሃ ባለፈ የከርሰ ምድር ውሃ አማራጮችን መለየትና መጠቀም ተገቢ መሆኑን በማንሳት።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የገጸ-ምድር አቀማመጥ ካርታ መሰረት ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ የከርሰ ምድር የውሃ ሀብቶች እንዳሏት መመላከቱን ጠቅሰዋል።

ድንበር ተሻጋሪ የከርሰ ምድር ውሃ ሃብቶችን ከጎረቤት አገራት ጋር በፍትሃዊነት ለመጠቀምና ተደጋጋሚ የውሃ እጥረት በሚያጋጥማቸው አካባቢዎች ጥቅም ላይ ለማዋል የውሃ ሃብቱን መገኛ በትክክል ማወቅ ተገቢ ነው ብለዋል።

በገጸ-ምድር ካርታው ይፋ የተደረጉ ውጤቶች ላይ ዝርዝር ጥናት በማድረግ የከርሰ ምድር ውሃ ሃብቱን ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚሰራም ነው ያነሱት።

የከርሰ ምድር ውሃ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያለውን የውሃ ፍላጎት በቀላሉ ለማሟላት የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም