ከውስብስብ ችግሮች መላቀቅ የምንችለው በሰለጠነ መንገድ መመካከርና መተባበር ስንችል ነው -ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ከውስብስብ ችግሮች መላቀቅ የምንችለው በሰለጠነ መንገድ መመካከርና መተባበር ስንችል ነው -ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)
ሶዶ ፤ጥቅምት 18/2017 (ኢዜአ):- እንደ ሀገር ከገባንበት ውስብስብ ችግሮች መላቀቅ የምንችለው በሰለጠነ መንገድ መመካከርና መተባበር ስንችል ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ማካሄድ ጀምሯል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት እንደ ሀገር ከገባንበት ውስብስብ ችግሮች መላቀቅ የምንችለው በሰለጠነ መንገድ መመካከርና መተባበር ስንችል ነው ።
ሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላምና ልማት በማረጋገጥ እንዲሁም የጋራ እሴቶችን በማጠናከር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
"ኮሚሽኑ የጋራ እሴቶችን ለመገንባት ብሎም አስተማማኝ ሰላምና ዕድገት ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል" ብለዋል።
ሀገራዊ ምክክር ሥራው የሁሉም ተሳታፊ ድምፅ የሚሰማበት፣ የመፍትሄ ሃሳቦች የሚደመጡበትና ሀገራዊ መግባባት የሚፈጠርበት መሆኑን ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር) ተናግረዋል ።
ኮሚሽኑ ባለፉት ጊዜያት በሰባት ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብና የውይይት ሥራን በስኬት ማጠናቀቁን አስረድተዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየተካሄደ ባለው አጀንዳ የማሰባሰብ ውይይት ከ12 ዞኖችና ከ96 ወረዳዎች ከሁለት ሺህ የሚልቁ የህብረተሰብ ተወካዮች እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ በሀገር ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን የማህበረሰብ ተወካዮችና መላው ህዝብ የበኩሉን እንዲወጣ ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገው የአጀንዳ ማሰባሰብና የውይይት መድረክ ለሚቅሉት ስድስት ቀናት እንደሚቆይ ተመላክቷል።
በአጀንዳ ማሰባሰቢያ የውይይት መድረኩ የኮሚሽኑ ሃላፊዎችን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የመንግስት አካላትና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተሳትፈዋል።