ኮሚሽኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የውይይት መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ ማካሄድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የውይይት መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ ማካሄድ ጀመረ
ሶዶ፤ ጥቅምት 18/2017 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የውይይት መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ ማካሄድ ጀመረ።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በዛሬው ውሎ አጀንዳ በማሰባሰብ ሂደት ዙሪያ በኮሚሽኑ በኩል ሰነድ ቀርቦ ውይይት ይደረጋል።
በመድረኩ በክልሉ ከ12 ዞኖችና ከ96 ወረዳዎች የተውጣጡ ሁለት ሺህ የሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ተሳታፊ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የመንግስት አካላት እንዲሁም ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ሌሎች ተሳታፊ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ዋናው ጊቢ እየተካሄደ ባለው የማስጀመሪያ መርሃ ግብር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች እና የኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።