ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማደግ ላይ ለሚገኙ አገራት ፍትሐዊ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር አበክሮ መስራት ይኖርበታል - የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማደግ ላይ ለሚገኙ አገራት ፍትሐዊ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር አበክሮ መስራት ይኖርበታል - የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2017 (ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ እና ሌሎች በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት ፍትሐዊ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ አበክሮ መስራት እንደሚገባው የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ አሳሰቡ።
በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ካለው የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን የቡድን ሰባት እና የአፍሪካ (G-7 Africa) የሚኒስትሮች ስብሰባ ተደርጓል።
በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በስብሰባው ላይ ተሳትፏል።
ጣልያን በፕሬዝዳንትነት የምትመራው የቡድን ሰባት የፋይናንስ ሚኒስትሮች በእዳ አስተዳዳር ላይ ያሉ ፈተናዎች፣ በአፍሪካ የፋርማሲዩቲካል አምራች ዘርፍ ላይ ያሉ ኢኒሼቲቮች፣ አረንጓዴ መሰረተ ልማት እንዲሁም ሁሉን አቀፍ እና የማይበገር የአቅርቦት ሰንሰለት አስመልክቶ ውይይት አድርገዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት ታሪካዊ እና ቆራጥነት የተሞላበት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞችን እየተገበረች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
ማሻሻያው የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተናዎችን ለመፍታት እና ከመንግስት መር ወደ ግል መር ኢንቨስትመንት በመሸጋገር ሚዛናዊ የእድገት ምንጭ መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።
ሪፎርሙ የአገር ውስጥ የሀብት መሰብሰብ አማራጭ ማስፋት፣ የወጪ አጠቃቀምን ለከት ለማስያዝ እና ጥብቅ የፊስካል ስርዓትን በመፍጠር ዘላቂ የፊስካል አስተዳደር ስርዓትን ማረጋገጥ እንደሚያስችል አመልክተዋል።
የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱን በገበያ እንዲመራ በማድረግ ያሉ ችግሮችን ለማስተካከል እንደሚረዳም ተናግረዋል።
የተቋማት እና በተለያዩ ዘርፎች እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎች ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ለስራ እድል ፈጠራ እና የኢኮኖሚ እድገትን ለማሳለጥ ምቹ መደላድል ይፈጥራል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
የኢትዮጵያ መንግስት ለዘላቂ እድገት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው ለኢትዮጵያ እና ሌሎች በማደግ ላይ ለሚገኙ አገራት ዝቅተኛ የወለድ ምጣኔ ያለው የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ እየተደረገ ላለው ድጋፍ ቀጣይነት ያለው ዓለም አቀፍ ትብብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በሚኒስትሮቹ ስብሰባ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአፍሪካ መር፣ አገር በቀል ለሆኑ ማሻሻያዎች እና የኢንቨስትመንት እቅዶች እንዲሁም የአፍሪካ አገራት አገር በቀል የፋይናንስ ማሰባሰብ አቅማቸውን በማጎልበት የፊስካል እፎይታ እንዲያገኙ እና የረጅም ጊዜ የልማት ስራቸውን ለመደገፍ እያከናወኑት ያለውን ስራ በተጠናከረ መልኩ እንዲደግፍ ጥሪ ቀርቧል።
በስብሰባው ላይ የቡድን ሰባት አባል አገራት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የአፍሪካ የፋይናንስ ሚኒስትሮች እና የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች መገኘታቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።