ከዘንድሮው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ለተሻለ ነገ የጋራ መፍትሄን እንጠብቃለን - ኢዜአ አማርኛ
ከዘንድሮው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ለተሻለ ነገ የጋራ መፍትሄን እንጠብቃለን

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2017(ኢዜአ)፦ከዘንድሮው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ለተሻለ ነገ የጋራ መፍትሄ እንደሚጠብቁ ወጣቶች ተናገሩ።
የአየር ንብረት ለውጥ የደቀነው አደጋ እና እያስከተለ ያለውን ቀውስ ተከትሎ ዓለም አቀፋዊ መፍትሔ ለማበጀት የዓለም መንግስታት በጉዳዩ ላይ መምከር ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
በመንግስታቱ ድርጅት የሚዘጋጀው ባለድርሻ አካላት ጉባዔ (ኮንፈረንስ ኦፍ ፓርቲስ) ደግሞ በዚህ ረገድ ግንባር ቀደሙ መድረክ ሲሆን ዘንድሮ ለ29ኛ ጊዜ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከህዳር 11 እስከ 22 ቀን 2024 በአዘርባጃን ባኩ ከተማ ይካሄዳል።
ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት የጀመረው የኮፕ ጉባዔ፤ ከዘመኑ ርቀት እና ከስብሰባዎች ብዛት አኳያ አመርቂ እርምጃ ባይመዘገብበትም አይነተ ብዙ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነቶችና ቃል ኪዳኖች ይፋ ተደርገውበታል፡፡
በሀገራት መሪዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ማህበረሰብ አንቂዎች፣ ለጋሽ ድርጅቶች በሚያሰባስበው የኮፕ መድረክ፤ የመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ የሚገዳቸው ታዳጊዎችና ወጣቶችም የራሳቸውን አጀንዳ ያስተጋባሉ።
በአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ተማሪዎች ምክር ቤት ጥምረት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተወካይ የሆነችው በጸሎት አበበ፤ ኮፕ ከስብሰባ ባሻገር መፍትሄ ተኮር ውጤቶች ማምጣት እንዳለበት ትገልጻለች።
በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በሚከሰቱ ቀውሶች ሴቶችና ህጻናት ዋነኞቹ ተጎጂዎች መሆናቸውን በመጥቀስ፤ የዘንድሮው ጉባዔ ተጋላጭ ማህበረሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ማድረግ አለበት ብላለች።
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆኑት ቤዛ መላኩ እና ናኦል ጌትነት በአዘርባጃን በሚካሄደው 29ኛው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ከሚሳተፉ ወጣቶች መካከል ናቸው።
የኮፕ አጀንዳዎች ሕፃናት፣ ሴቶችና ወጣቶችን ጨምሮ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለሁለንተናዊ ቀውሶች የሚዳረጉ ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎችን ያማከሉ መሆን እንደሚገባቸው ይናገራሉ።
በዚህም የዘንድሮው የኮፕ-29 ጉባዔ ድምጽ አልባ የማህበረሰብ ክፍሎች ድምጻቸው እንዲሰማ ይሻሉ።
ሶስት አስርት ዓመታት የተሻገረው የኮፕ ጉባዔ ከስብሰባ ባለፈ ተጨባጭ የመፍትሄ እርምጃዎች ላይ መድረስ እንዳለበትም ይናገራሉ፡፡
ለአብነትም ለታዳጊ ሀገራት ቃል የተገባው የፋይናንስ ድጋፎችን ወደ ተግባር መለወጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የዘንድሮው ጉባዔ መፍትሔ ተኮር ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።