ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚያካሂደውን የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ በነገው ዕለት በይፋ ይጀምራል

ሶዶ፤ ጥቅምት 17/2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚያከናውነውን የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ነገ ጥቅምት 18/2017 በይፋ እንደሚጀምር ገለጸ።

ኮሚሽኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚያደርገውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ከነገ ጀምሮ በወላይታ ሶዶ ከተማ እንደሚያካሂድ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚያካሂደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ተግባር ዙሪያ ዛሬ በሶዶ ከተማ መግለጫ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ በምክክር ላይ በመመስረት ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማሻገር ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል።

ኮሚሽኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚያከናውነውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ከነገ ጀምሮ የህብረተሰብ ተወካዮችና ሌሎች አካላት በተገኙበት በወላይታ ሶዶ ከተማ ማካሄድ እንደሚምጀምር ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩም የአጀንዳ ማሰባሰብና የሀገራዊ ምክክሩ ተሳታፊዎች ምርጫ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

በዚህም ከዚህ ቀደም ከክልሉ ከ12 ዞኖች የተመረጡ የህብረተሰብ ተወካዮች ያሰባሰቡትን አጀንዳ ያቀርባሉ ብለዋል።

ከነገ ጥቅምት 18/2017 ዓ.ም ጀምሮ በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ከ96 ወረዳዎች የተመረጡ የህብረተሰብ ወኪሎችን ጨምሮ ከ2 ሺህ በላይ ተወካዮች እንደሚሳተፉ በመግለጫው አንስተዋል።

መርሃ ግብሩም ለሚቀጥሉት ስድስት ቀናት እንደሚቆይም ጠቁመዋል።

በመድረኩም የተመረጡ የህብረተሰብ ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የመንግስት አካላት እንዲሁም ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ሌሎች እንደሚገኙም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም