የደሴ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እያከናወናቸው ያሉት ተግባራት ልምድ የሚወሰድባቸው መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የደሴ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እያከናወናቸው ያሉት ተግባራት ልምድ የሚወሰድባቸው መሆኑ ተገለጸ

ደሴ/መተማ ፤ ጥቅምት 17/2017(ኢዜአ)፡- የደሴ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በየደረጃው ለመመልስ እያከናወናቸው ያሉት ተግባራት ልምድ የሚወሰድባቸው መሆኑ ተገለጸ።
"የህልም ጉልበት ለእመርታዊ እድገት" በሚል መሪ ሀሳብ በደሴና ገንዳ ውሃ ከተሞች ስልጠና እየወሰዱ የሚገኙ የአመራር አባላት የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
የደሴውን ስልጠና እያስተባበሩ ያሉት አቶ ባዘዘው ጫኔ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለፁት፤ የአመራሩን አቅም በማጎልበት የክልሉን ህዝብ ሁለተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው።
ለዚህም በተለያዩ ከተሞች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው፤ በተጓዳኝ የከተሞችን የልማት ስራ በማስጎብኘት የልምድ ልውውጥ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዚህም በደሴ ከተማ የብልጽግና ጉዞውን የሚያረጋግጡ አስደናቂ የልማት ስራዎች መመልከታቸውን ጠቅስው፤ አመራሩ ከደሴ ከተማ ልምድ ወስዶ የአካባቢው ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄን በየደረጃው ሊመልስ እንደሚገባ ተናግረዋል።
"በተለይም ህብረተሰቡን በማስተባበር ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ በጥራት የመጨረስ ልምዱን መውሰድና የአካባቢውን ሁለተናዊ ልማትና ብልጽግና ሊያረጋግጥ ይገባል" ብለዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፤ ህብረተሰቡን በማስተባበር የተሰሩ ልማቶች አበረታችና ልምድ የሚወሰድባቸው ናቸው ብለዋል።
በተለይም በስማርት ሲቲ፣ በኮሪደር ልማትና በሌሎችም ተስፋ ሰጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ በተያዘው በጀት ዓመትም ሰፋፊ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አስናቀ ጥላሁን እንዳሉት፤ በደሴ ከተማ የተገነቡ መስረተ ልማቶች ልምድ የተገኘባቸው ናቸው።
"በደሴ ከተማ የተመለከትነው ልማት እኛንም ያነቃቃ ነው" ያሉት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ ዓሊ ሁሴን ናቸው።
የአመራር አባላቱ የደሴ መናኸሪያ ግንባታ፣ የአስፋልት መንገድ፣ የኮሪደር ልማት፣ የስማርት ሲቲ ልማትና ሌሎችንም ትጎብኝተዋል።
በተመሳሳይ በገንደ ውሃ ከተማ በስልጠና ላይ ያሉ የአመራር አባላት የከተማውን የልማት ፕሮጀክቶች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳደር የህዝብ አደረጃጀትና ተሳትፎ አማካሪ አቶ እያሱ ይላቅ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ዞኑ ያለውን የተፈጥሮ ሀብትና አቅም በመጠቀም የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ይሰራል።
ከለውጡ ወዲሁ በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች በዞኑ መከናወናቸውን አንስተው፤ ሆኖም የህዝቡን ጥያቄ በበቂ ሁኔታ ለመመለስ በስልጠና የተገኘውን አቅምና ልምድ በመውሰድ መስራት ይገባል ብለዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ አብዱልከሪም ሙሐመድ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የከተማውን እድገት የሚያፋጥኑ እና የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት በስፋት እየተተገበሩ ናቸው።
በዚህም በተለይም ወጣቱን በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፍ ተጠቃሚ የሚያደርጉ፤ በአካላዊና ስነልቦናዊ እድገት አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ተግባራት መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል።
የስልጠናው ተሳታፊ ወይዘሮ ፍሬህይወት ምስጋናው በሰጡት አስተያየት፤ በገንዳ ውኃ ከተማ የተሰሩ የልማት ተግባራት ወደ አካባቢያቸው በመውስድ ህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
"በስልጠና እና ጉብኝቱ ያገኘሁትን ጠቃሚ ዕውቀት ወደ አካባቢዬ ስመለስ ወደ ተግባር በመቀየር የህዝቡን የልማትና የመልካም አሰተዳደር ጥያቄ ለመመለስ ተዘጋጅቻለሁ" ያሉት ደግሞ የመተማ ወረዳ አመራር አባል አቶ ምህረት አበበ ናቸው።