በጎንደርና ደብረማርቆስ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጎላ ፋይዳ እንዳላቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደርና ደብረማርቆስ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጎላ ፋይዳ እንዳላቸው ተገለጸ
ጎንደር/ደብረማርቆስ፤ ጥቅምት 17/2017(ኢዜአ)፡- በጎንደርና ደብረማርቆስ ከተሞች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጎላ ፋይዳ እንዳላቸው ተገለጸ።
በጎንደርና ደብር ማርቆስ ክተሞች የ3ኛው ዙር ሰልጣኝ አመራር አባላት የከተሞችን የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችንና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል።
ከጎንደር ከተማ ሰልጣኞች መካከል አቶ አዛናው አደባ እንዳሉት፤ የከተማው ሁለገብ የልማት ስራዎች መንግስት ለከተሞች ኢኮኖሚያዊ እድገት የሰጠው ልዩ ትኩረት ማሳያ ነው፡፡
እነዚህ የልማት ተሞክሮዎች አመራሩ ወደ አካባቢው ሲመለስ የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች በላቀ ቁርጠኝነት ምላሽ ለመስጠት መነቃቃትና ቁጭት የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል፡፡
በሌማት ትሩፋት ፣በከተማ ግብር፣ በኢንቨስትመንትና በመሰረተ ልማት ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ተግባራት የመንግስት የብዝሃ ኢኮኖሚ ግንባታ ማሳያ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው ሰልጣኝ አቶ ሰለሞን መሳፍንት ናቸው፡፡
የአካባቢን የተፈጥሮ ጸጋዎች ለይቶ በማልማት ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠርና የህዝብንም የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በየደረጃው የምንገኝ አመራሮች የወቅቱ ቀዳሚ ተልዕኮና ተግባራችን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ሌላው ሰልጣኝ አመራር አቶ ሀብቴ ተስፋ ፤ የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማት ስራ አነስተኛና መካከለኛ ከተሞች በሞዴልነት ወስደው ሊተገብሩት የሚገባ ምርጥ የልማት ተሞክሮ ነው ብለዋል፡፡
የጎንደር ስልጠና ማዕከል አስተባባሪና የክልሉ የመሬት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ እንዳመለከቱት፤ ስልጠናው አመራር አባላት የተግባርና የአመለካከት አንድነትን በማጠናከር በኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ዘርፍ የተመዘገቡ ድሎችን እንዲያስቀጥሉ ለማስቻል የተሰናዳ ነውው፡፡
በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማትና የቅርስ ጥገና ስራዎች መንግስት ታሪክንና ባህልን በመጠበቅ ለትውልድ ለማሻገር ያላውን ቁርጠኝነት ያረጋገጡበት ነው ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በደብረ ማርቆስ ከተማ ጉብኝት ውቅት የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ እንደገለጹት፤ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን ለማነሳሳትና ለመደገፋ ርብርብ እየተደረገ ነው።
የከተማን ብልጽግና መረጋገጥ የሚቻለው የልማት አውታሮችን መደገፍ እና ማሳለጥ ሲቻል እንደሆነ ጠቅስው፤ ባለሀብቶችን መሳብ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ተመስገን ተድላ በበኩላቸው፤ በከተማ አስተዳደሩ በኢንዱስትሪ መንደር ከ170 በላይ ፕሮጅክቶች ይገኛሉ ብለዋል።
ከመካከላቸውም 28 በማምረት ላይ ያሉ፣ 40 ፕሮጀክቶች ለማምረት የተዘጋጁና ቀሪዎች ደግሞ በግንባታ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የንጋት ኮርፖሬት የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የግብዓት አቅርቦት አስተባባሪ አቶ አለኸኝ አበበ እንዳሉት፤ ፋብሪካው በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጭ የሚገነባ ሲሁን፤ አሁን የማሽን ተከላ እየተከናወነ ነው።
ፋብሪካው ቀሪ ስራዎችን በማጠናቀቅ እስከ የካቲት ወር 2017 ዓ.ም ማምረት እንደሚጀምር ጠቁመዋል።
በጉብኝቱ የተሳተፉት ወይዘሮ አበባ ፈንቴ በሰጡት አስተያየት፤ የከተማው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የሚያበረታታ ነው ብለዋል።