ቀጥታ፡

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አርሰናል እና ሊቨርፑል የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2017(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዘጠነኛ ሳምንት መርሃ ግብር አርሰናል እና ሊቨርፑል ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ30 በኤምሬትስ ስታዲየም ይካሄዳል።

አርሰናል በዘንድሮው የውድድር ዓመት ባደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፎ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይቷል።

መድፈኞቹ በጨዋታዎቹ 15 ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ስምንት ግቦችን አስተናግደው በ17 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ተጋጣሚው ሊቨርፑል በሊጉ ባደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች ሰባት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፎ 15 ግቦችን ሲያስቆጥሩ ሶስት ግቦችን በማስተናገድ በ21 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

የ42 ዓመቱ ስፔናዊ የአርሰናሉ አሰልጣኝ ማይክል አርቴታ ከሊቨርፑል ጋር በሚኖረን ጨዋታ ልዩ የሆነውን አርሰናል ጠብቁ፣ ግጥሚያውን በድል እንወጣለን ሲል ከጨዋታው በፊት አስተያየቱን ሰጥቷል። 

በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ቢጎዱብንም ቡድኑ ባለው ጠንካራ መንፈስ እና ብቃት ያሉብንን ፈተናዎች እናልፋለን ብሏል።

የ46 ዓመቱ ኔዘርላንዳዊ የሊቨርፑል አሰልጣኝ አርን ስሎት ጊዜው ገና ቢሆንም እንደ አርሰናል ያለውን የዋንጫ ተፎካካሪ ቡድን ማሸነፍ በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከሜዳችን ውጪ ጨዋታውን ማድረጋችን ቢፈትነንም ተጫዋቾቼ በእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ውስጥ የማለፍ ልምድ አላቸው ሲሉ ተናግረዋል።

በዛሬው ጨዋታ የአርሰናል አምባል ማርቲን ኦዴጋርድ እና በቦርንማውዙ ጨዋታ ቀይ ካርድ የተመለከተው ዊሊያም ሳሊባ በጨዋታው እንደማይሰለፉ ተረጋግጧል።

ቡካዮ ሳካ፣ ጁሪየን ቲምበር እና ሪካርዶ ካላፊዮሪ ወደ ልምምድ ቢመለሱም የመሰለፋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል።

በሊቨርፑል በኩል ግብ ጠባቂው አሊሰን ቤከር እና አጥቂው ዲያጎ ጆታ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም።

አርሰናል እና ሊቨርፑል በሁሉም ውድድሮች እስከ አሁን 242 ጊዜ ተገናኝተዋል። 

ሊቨርፑል 95 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ አርሰናል በበኩሉ 83 ጊዜ ሲያሸንፍ 64 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። 

ዘንድሮ አስደናቂ ጅማሮ ያሳየው ሊቨርፑል እና የሊጉን ዋንጫ ያነሳል ተብሎ ግምት እየተሰጠው የሚገኘው አርሰናል የሚያደርጉት ጨዋታ የተመልካቾችን ቀልብ ይበልጥ ስቧል።

የእግር ኳስ ተንታኞች የጨዋታው ውጤት የዋንጫ ፉክክሩን ለመወሰን ገና ቢሆንም በፉክክሩ ላይ የራሱ ተጽእኖ እንደሚኖረው በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።

የ46 ዓመቱ አንቶኒ ቴይለር የሁለቱን ቡድኖች ተጠባቂ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

በተያያዘም ትናንት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በተካሄደ የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ ሳውዝሀምፕተንን 1 ለ 0 በማሸነፍ በ23 ነጥብ የሊጉ መሪ መሆን ችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም