በክልሉ የጨቅላ ህፃናት ማሞቂያ ማዕከል በጤና ተቋማት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የጨቅላ ህፃናት ማሞቂያ ማዕከል በጤና ተቋማት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዳማ ፤ጥቅምት 17/2017 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚያስችል ያለጊዜ የተወለዱ ህፃናት ማሞቂያ ማዕከል በጤና ተቋማት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።
የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ከጤና ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በክልሉ የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የሚያስችሉ የህክምና ማዕከላትና ግብዓት ለማሟላት የሚያስችል ፕሮጀክት ዛሬ በአዳማ ይፋ አድርጓል።
በመድረኩ ላይ በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣ ህፃናትና አፍላ ወጣቶች ጤና አገልግሎት መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አለማየሁ ሁንዱማ እንዳሉት፤ የጨቅላ ህፃናት ሞትን ለመቀነስ ማህበረሰቡን ከማንቃት ጀምሮ የግንዛቤ እጥረት ለመፍታት እየሰሩ ነው።
በተለይም እናቶች በምጥ ጊዜ ፈጥነው ወደ ጤና ተቋማት እንዲደርሱ የትራንስፖርት አገልግሎት ችግር እንዳይኖር አምቡላንሶችን ተደራሽ የማድረግ እንዲሁም ፈጣንና ጥራት ያለው ህክምና በወቅቱ እንዲያገኙ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ከጨቅላ ህፃናት ማሞቂያ በተጨማሪ የፅኑ ህሙማን የህክምና መርጃ ማእከልን ለማደራጀትና በህክምና ቁሳቁስ ለማሟላት እንዲሁም የጨቅላ ህፃናት ሞት መንስኤዎችን በጥናትና ምርምር ለመለየት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል።
የጨቅላ ህፃናት ኢንፌክሽንና የመታፈን ችግሮችን ለይተን ከሰራን 90 በመቶ የሚሆነው ያለጊዜ የሚወለዱና የጨቅላ ህፃናትን የጤና ችግር እንፈታለን ያሉት ዶክተር አለማየሁ፤ ለዚህም ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በጀት መመደቡንም ጨምረው ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደረጀ አብደና በበኩላቸው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጨቅላ ህጻናትን ሞት ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ በክልሉ እናቶች ጥራት ያለውና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ እየሰራን ነው።
በክልሉ ያሉ የጤና ተቋማትም ለእናቶች ጤና ትኩረት በመስጠት በቅድመ ወሊድና ድህረ ወልድ ተገቢውን አገልግሎት በወቅቱ እንዲሰጡ፣ ምልልስ እንዳይኖር፣ በቂ የሰው ሃይል፣ መድሃኒትና የህክምና መሣሪያዎች እንዲሟላ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የጨቅላ ህፃናት ሞት ትልቁ መንስኤ ኢንፌክሽንና መታፈን በመሆኑ ህጻናት እንደተወለዱ ቀልጣፋና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ማግኘት እንዳለባቸው ገልጸው፤ ለዚህም የጨቅላ ህፃናት ማሞቂያ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራን ነው ብለዋል።
በተለይም ያለጊዜ የሚወለዱ ጨቅላ ህፃናትን ህይወት ለመታደግ በጤና ተቋማቱ የጨቅላ ህፃናት ማሞቂያ ማዕከል ከ50 በላይ በሚሆኑ የክልሉ ሆስፒታሎች ማደራጀቱን ገልፀው፤ በቀሪዎቹ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም ዛሬ ይፋ በተደረገው ፕሮጀክት በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ እስከ 108 የሚደርሱ ሆስፒታሎች የጨቅላ ህፃናት ህክምናና ማሞቂያ ማእከል እንዲኖራቸው ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።
"የእናቶችና ጨቅላ ህፃናት ጤናን ለይተን ማየት አንችልም" ያሉት ምክትል ኃላፊው፤ ''ህፃናት የኢንፌክሽንና የመታፈን ችግሮች እንዳይገጥማቸው ተገቢ የሆነ ክትትልና ህክምና እንዲያገኙ ይደረጋል'' ነው ያሉት።