በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ በተደጋጋሚ የሚፈጸም ስርቆት በኃይል ልማትና ተደራሽነት ላይ እንቅፋት ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ በተደጋጋሚ የሚፈጸም ስርቆት በኃይል ልማትና ተደራሽነት ላይ እንቅፋት ሆኗል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2017(ኢዜአ)፦ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ በተደጋጋሚ የሚፈጸም ስርቆት በኃይል ልማትና ተደራሽነት ላይ እንቅፋት መፍጠሩን የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኃይል ገለጸ።
በ2016 በጀት ዓመት ብቻ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ሃብት ስርቆት ተፈፅሟል ተብሏል።
የኃይል ልማት ለአንድ ሀገር የምጣኔ ሃብት እድገት መሳለጥ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል።
የሃይል አቅርቦት ለኢንዱስትሪ ምርታማነት፣ ለቀልጣፋና አስተማማኝ አገልግሎት አሰጣጥና አጠቃላይ ለሰዎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የማይተካ ሚና እንዳለውም ይታመናል።
በኢትዮጵያም የምጣኔ ሃብት ዕድገቱን ተከትሎ የኃይል አቅርቦት ፍላጎቱ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ በመምጣቱ በዚሁ መሰረት ለሃይል ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።
የኃይል አማራጮችን በማስፋት በተለይም በታዳሽ የሃይል ልማት ላይ በስፋት እየተሰራ ሲሆን በሂደቱ ፈታኝ ነገሮች እንዳሉም ይነሳል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን፤ ለሃይል ልማት መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይልን ከማምረት ጀምሮ መሰረተ ልማቶችን የማስፋትና ተደራሽ የማድረግ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውንም ተናግረዋል።
በዚህ የተጠናከረ የልማት ሂደት ውስጥ ግን በስርቆትና ሌሎችም ምክንያቶች በመሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳቶች እየተስተዋሉ እንዳሉ አንስተዋል።
ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ የተደረገባቸው የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች በተደጋጋሚ ስርቆት ሳቢያ በኃይል ልማትና ተደራሽነት ላይ እንቅፋት ሆኖ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በማሳያነት ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ሃብት መሰረቁን አንስተው ለዚህም መልሶ ግንባታ 200 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ነው የተናገሩ።
በመሆኑም እንዲህ አይነት የልማት ጠንቅ የሆኑ ችግሮችን መከላከል የጋራ ጥረታችን ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በዘርፉ መሰረተ ልማት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ተቋሙ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እያደረገ ያለውን ቅንጅታዊ ስራ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።