ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ከእንስሳት ኃብት የሚገኘውን አገራዊ ገቢ ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሰሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ከእንስሳት ኃብት የሚገኘውን አገራዊ ገቢ ለማሳደግ የእንስሳት ጤናና ደኅንነት ለመጠበቅ የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።  

የግብርና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ለ14ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ99ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለም የእንስሳት ቀን በማስመልከት ከተለያዩ አጋር አካላት ውይይት አካሂዷል።



 

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ጤና መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ውብሸት ዘውዴ፤ የእንስሳት ጤና ለመጠበቅ፣ ደኅንነት ለማረጋገጥና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

በተለይም ከዘርፉ የሚገኘውን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ለአገር የሚያስገኙትን ጠቀሜታ የበለጠ ለማስፋት በሌማት ትሩፋት ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

አገልግሎት የሚሰጡ የጋማ እንስሳቶችን ጨምሮ የእንስሳት ደኅንነትን ለመጠበቅም  አበረታች ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በድምሩም የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል። 


 

የኢትዮጵያ እንስሳት ሐኪም ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ቦጃ እንደቡ በበኩላቸው ማኅበሩ የእንስሳት ሕክምና፣ ምርምርና ግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በእንስሳት ላይ የሚከሰቱ የተለያዩ በሽታዎችን ህክምና እየሰጡ መሆኑን ጠቁመው የእንስሳትን ጤና መጠበቅ በተዘዋዋሪ የሰውን ጤና መጠበቅ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህንንም ከግምት በማስገባት የእንስሳት ክብካቤና አጠቃቀም ላይ የግንዛቤ ሥራዎች በስፋት እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው ይህም በቀጣይ ሊጠናከር እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት። 

በኢትዮጵያ ያለውን በጋማ አንሰሳት ላይ የሚስተዋለውን የሥራ ጫናም ሆነ የደኅንነት ሁኔታን ለማሻሻል የግንዛቤ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢስፓና ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ኃላፊ ዶክተር ሃና ዘውዱ ናቸው።


 

ድርጅታቸው ከመንግሥት የጤና ተቋማት ጋር በመሆኑን የክትባትና የግንዛቤ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ባለቤት አልባ የሆኑ ውሾችን ክትባት በመስጠት በሰው ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የጀርመኑ ቪ ኤስ ኤፍ የተሰኘው ድርጅት የውሻ እብደት በሽታ መከላከል የአዲስ አበባ አስተባባሪ ዶክተር ይመስገን ታረቀኝ ናቸው።

በዚህም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር የውሾች ክትባት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም