ቀጥታ፡

በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የተመራው ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲና ከእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2017(ኢዜአ)፦ በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የተመራው ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲና ከእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት የስራ ኃላፊዎች ጋር መወያየቱ ተገለጸ።

እየተካሄደ ካለው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ አመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ከእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ (AIIB) ፕሬዝዳንት ጂን ሊኩን እና ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ (AFD) ዋና ዳይሬክተር ሬሚ ሪዮክስ ጋር ተወያይተዋል።


 

በውይይታቸውም በተለያዩ የትብብርና የልማት ስራዎች ድጋፍ ዙሪያ የመከሩ ሲሆን በተለይ ሚኒስትሩ ከፕሬዚዳንት ሊኩን ጋር ባደረጉት ምክክር ባንኩ ለመሠረተ ልማት የሚሆን ኮንሴንሽናል ፋይናንስ በሚሰጥበት አግባብና ቀጣይ የትብብር ስራዎች ላይ በሰፊው መወያየታቸው ተገልጿል::

በዚህ ረገድ ፕሬዝዳንት ሊኩን ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ እና ከአውሮፓ ህብረት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የኢነርጂ ፕሮጀክቶችን እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በቢሾፍቱ ለመገንባት ላሰበው ግዙፍ ኤርፖርት ፋይናንስ የሚደረግበትን ሁኔታ በቀጣይ ለማየት ከስምምነት መደረሱም ተመላክቷል።

በተጨማሪም ሚኒስትሩ ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ (AFD) ዋና ዳይሬክተር ሬሚ ሪዮክስ ጋር በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ስላሉ የልማት ስራዎች ተወያይተዋል።

በነበራቸው ቆይታም የፈረንሳይ መንግስት በተለይ ለኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ስለሚሰጠው ተጨማሪ ድጋፍ መክረዋል።

በቀጣይም በሁለትዮሽ ትብብር የሚደረገው እገዛ ተጠናክሮ ስለሚቀጥልበት አግባብም መወያየታቸው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም