ጨቅላ ህፃናትን መታደግ (ሴቭ ሊትል ላይቭ) የሚል አዲስ መርሃግብር በትግራይ ክልል አራት ሆስፒታሎች ሊተገበር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጨቅላ ህፃናትን መታደግ (ሴቭ ሊትል ላይቭ) የሚል አዲስ መርሃግብር በትግራይ ክልል አራት ሆስፒታሎች ሊተገበር ነው

መቀሌ ፤ጥቅምት 16/2017(ኢዜአ)፦ ጨቅላ ህፃናትን መታደግ (ሴቭ ሊትል ላይቭ) የሚል አዲስ መርሃግብር በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር በአራት ሆስፒታሎች ተግባራዊ እንደሚደረግ የጊዚያዊ አስተዳደሩ የጤና ቢሮ ገለፀ።
ይህንኑ መርሃ ግብር ተግባራዊ ለማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀሌ ከተማ ዛሬ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
ጊዚያዊ አስተዳደሩ የጤና ቢሮ የእናቶችና ህፃናት ጤና እንክብካቤ ባለሙያ አቶ ሀፍቱ ሀይለኪሮስ እንደገለፁት፤ በክልሉ የሚያጋጥምን የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየተሰራ ነው።
በአራት የክልሉ ሆስፒታሎች ተግባራዊ የሚሆነው አዲሱ መርሃግብር የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በሌላ መርሃ ግብርና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች በተገኘው ድጋፍ በ32 ሆስፒታሎች የእናቶችና ህፃናት ሞት ለመቀነስ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
አሁን ደግሞ ከኤን.ኢ.ኤስ.ቲ 360 (NEST 360) በተገኘ ድጋፍ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በዓይደር ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና በመቀሌ አጠቃላይ ሆስፒታል እንዲሁም በሀገረሰላምና ዓዲጉደም መለስተኛ ሆስፒታሎች መርሃ ግብሩን ተግባራዊ ለማድረግ መታቀዱ አገልግሎቱ ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆን እንደሚያደረግ አብራርተዋል።
በመቀሌ ዩኑቨርሲቲ ከኤን.ኢ.ኤስ.ቲ 360 ሪጅናል ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ታደለ ተስፈአን በበኩላቸው፤ ከጤና ሚኒስቴርና የክልል ጤና ቢሮዎች በመተባበር በተለያዩ ሆስፒታሎች የጨቅላ ህፃናት ሞት ለመቀነስ የሚያስችል መርሃ ግብር ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በትግራይ በአራቱ ሆስፒታሎች ለአምስት ዓመታት ተግባራዊ በሚደረገው መርሃ ግብር የሰው ሃይል በማብቃት የህክምና መሳሪያና መድሐኒት በማቅረብ ለእናቶችና ህፃናት ጥራት ያለውን የህክምና አገልግሎት በመስጠት ውጤታማ ስራ እንደሚሰራ አብራርተዋል።
የሀገረሰላም መለስተኛ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ራህዋ ዮሃንስ ጨቅላ ህፃናት መታፈን፣ ኢንፌክሽን እና ጊዜያቸው ሳይደርስ የሚወለዱ ህፃናት፣ ለጨቅላ ህፃናት ሞት ዋነኛ ምክንያት ተብለው በውይይቱ መለየታቸውን ጠቁመዋል።
የቅድመ ወሊድ ክትትል አለማድረግ፣ በጤና ተቋማት አለመውለድና ቢወለዱም በቂ እና ጥራት ያለው አገልግሎት አለማግኘት ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን የገለፁት ዶክተር ራህዋ፤ ሆስፒታሉ የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ መሆኑ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንደሚፈታላቸው ተናግረዋል።
በዓይደር ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የነርስ ትምህርት ከፍል ሃላፊ ካሌብ ብርሀኑ በበኩላቸው፤ የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
የመርሃ ግብሩ መጀመር ሆስፒታሉ የህክምናና ቁሳቁስ በሟሟላት በእናቶችና ህፃናት እየሰጠ ያለው የጤና አገልግሎት ለማሳደግ ያግዘዋል ብለዋል።