በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች ከተማዋ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ምቹ እንድትሆን ትልቅ ዕድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች ከተማዋ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ምቹ እንድትሆን ትልቅ ዕድል ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 16/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች ከተማዋ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ምቹ እንድትሆን ትልቅ ዕድል መፍጠሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።
ከለውጡ ወዲህ የከተማዋን የቱሪዝም ልማት ሥራዎች ለማስፋት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።
ከእነዚህም መካከል አንድነት ፓርክ፣ እንጦጦ ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ፣ የአድዋ ድል መታሰቢያና ሌሎች ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የተሰሩ ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው።
በአዲስ አበባ በተለያዩ አከባቢዎች እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማትም ከተማዋን በማደስ የተለየ ገጽታ እንድትላበስ ያስቻለ ሌላው ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሐፍታይ ገብረ እግዚአብሔር ፤ አዲስ አበባን ወደ ኮንፈረንስ ቱሪዝም ከተማነት የማሸጋገር ዕቅድ ተይዞ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በመዲናዋ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የቱሪዝም ኃብቶች እንዲገለጡ፣ ይበልጥ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማስቻላቸውን አስረድተዋል።
ይህንንም ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማ አሁን ላይ በርካታ የዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ስበሰባዎችን ለማከናወን ቀዳሚ ተመራጭ እየሆነች መምጣቷን ገልጸዋል።
በቅርብ ጊዜያት የተከናወኑ የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ስብሰባ፣ ዓለም አቀፍ የፈጠራ ውድድሮች፣ የካፍ ጉባዔን ጨምሮ የከተሞች ፎርምን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በዚህም የተከናወኑና በመከናወን ላይ የሚገኙ የልማት ተግባራት መዲናዋ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ምቹ ከተማ እንድትሆን ማስቻሉንም ጠቁመዋል።
በአድዋ ድል መታሰቢያ ውስጥ የተገነቡ ትልልቅ የመሰብሰቢያ አደራሾችም ከተማዋ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ኮንፈረንስ እንድትሆን ትልቅ አስተዋጽ ማበርከቱንም ጠቁመዋል።
ለቱሪዝም ኮንፈረንሱ ዘርፍ ይበልጥ መጎልበትም መንግሥት ከሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች ባሻገር የግሉ ዘርፍ ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል።
ከተማዋን በዓለም አቀፍ መድረኮች ይበልጥ በማስተዋወቅ ረገድ ሁሉም የበኩልን ሊወጣ እንደሚገባም ጠቁመዋል።