ቀጥታ፡

በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገሊላ ማኑፋክቸሪንግ ኩባንያ ያስገነባው የጫማ ማምረቻ ፋብሪካ ስራ ጀመረ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 16/2017(ኢዜአ)፦በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ  ገሊላ ማኑፋክቸሪንግ የተሰኘ ሀገር በቀል ኩባንያ ያስገነባው የጫማ ማምረቻ ፋብሪካ ስራ ጀመረ ።

ፋብሪካው በቀን ከ2 ሺህ እስከ 4 ሺህ የተለያዩ ጫማዎችን በማምረት ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ እንደሚያቀርብ የተገለጸ ሲሆን ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ተነግሯል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን  የሰው ሀብት ዘርፍ  ምክትል  ዋና ስራ አስፈፃሚ አለማየሁ ሰይፉ እንደገለፁት፣ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው እንዲያለሙ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው።

በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተከፈቱ ፋብሪካዎችም ከ27 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልፀዋል።

የገሊላ ማኑፋክቸሪንግ በይፋ ስራ ያስጀመረው የጫማ ማምረቻ በጥራት ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ለገበያ ማቅረብ እንዳለበት ገልጸው፥ ፋብሪካዎች ጥራት ያለው ምርት እንዲያቀርቡ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የገሊላ ማኑፋክቸሪንግ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ  በርሄ አሰፋ በተለያዩ የአምራች ዘርፎች በመሰማራት የተለያዩ  ጥራት ያላቸው  ምርቶችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፥ ዛሬ ባስጀመሩት የጫማ ፋብሪካም ከራስ አልፎ ለሀገር የሚጠቅም ስራ እንደሚያከናውኑ ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም