ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የማሌዢያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 16/2017(ኢዜአ)፦ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የማሌዢያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎችን ተጠቅመው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሚኒስትሮች ልዑካን ቡድን ጋር በመሆን በማሌዢያ ኳላላምፑር ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው፥ ከማሌዢያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም ጋር ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ እና ማሌዢያ ለረጅም ጊዜ የቆየ የሁለትዮሽ ትብብር እና ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ፍሬያማ ውይይት መደረጉን አመልክተዋል።


 

ሀገራቱ በግብርና፣ኢንዱስትሪ፣ማዕድን፣ንግድ እና ኢንቨስትመንት ጨምሮ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ማጎልበት የሚችሉባቸው ብዙ እድሎች እንዳሉም አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የማሌዢያ ባለሀብቶች የኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ይዞ የመጣውን የኢንቨስትመንት እድል በመጠቀም መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።

የማሌዢያ የንግዱ ማህበረሰብ እና የግሉ ዘርፍ በኢንቨስትመንት ላይ ለሚያደርገው ተሳትፎ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከማሌዢያ በፌደራል ስርዓት፣በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ እና ከተሞችን በማዘመን ስራ ልምድ መቅሰም እንደምትፈልግም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የማሌዢያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።

የማሌዢያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ሁለቱ ሀገራት በንግድ፣ ኢኮኖሚ፣ የምግብ ቴክኖሎጂ፣ ኢነርጂ እና በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ማሌዢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማጎልበት እንደምትሰራ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ወሳኝ አጋር እና የአፍሪካ መግቢያ በር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በኢትዮጵያ አስደናቂ ለውጥ እና እድገት እየታየ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በኢኮኖሚ፣መልካም አስተዳደር ማስፈን ፣ ሙስናን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ጥረት፣የትምህርት ጥራት፣የኢትዮጵያ አየር መንገድ እድገት እና በሌሎች መስኮች እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦችን አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከሚገኙ ግዙፍ አገራት አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፥ ለአፍሪካውያን አንድነት እና ትብብር ትልቅ ሚና እንደተወጣች ገልጸዋል።

ማሌዢያ በኢትዮጵያ ከመጡ ለውጦች ልምድ ለመቅሰም እና የራሷን ተሞክሮዎችም ለማጋራት ዝግጁ ናት ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ኢትዮጵያ ማሌዢያ የብሪክስ አጋር አገር እንድትሆን ላደረጋቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም