ቀጥታ፡

ቦርዱ ሴት አባላት ሳይኖራቸው አለን በማለት ገንዘብ የተቀበሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማገዱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2017(ኢዜአ)፦ ሴት አባላት ሳይኖራቸው አለን በማለት በሀሰተኛ ሪፖርት ገንዘብ የተቀበሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማገዱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ በቅርቡ በተሻሻለው የፓርቲዎች አገልግሎት እና ምዝገባ ክፍያ እንዲሁም እገዳ በተጣለባቸው ፓርቲዎች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አቶ ውብእሸት እንዳሉት ቦርዱ በፓርቲዎች ውስጥ የሚሳተፉ ሴቶችን እንዲሁም አካል ጉዳተኞችን ለማበረታታት ለፓርቲዎች ገንዘብ የሚሰጥበት አሰራር ዘርግቷል።

ይሁን እንጂ ለማበረታቻ ከቦርዱ የሚበጀተውን ገንዘብ አላግባብ ለመጠቀም የሌላቸውን አባላት ቁጥር አለን በማለት የሚያቀርቡ ፓርቲዎች መኖራቸው ተረጋግጧል ነው ያሉት።

ቦርዱ ባደረገው ማጣራት የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ አገው ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ የሌላቸውን ሴት አባላት ቁጥር አለን በማለት የሃሰት ሪፖርት በማቅረብ ገንዘብ በመቀበል ህገ ወጥ ተግባር በመፈጸማቸው የዕግድ ውሳኔ እንደተላለፈባቸው አብራርተዋል።

ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ሌሎች ተጨማሪ ፓርቲዎች ላይም እርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል።

እንደ ምክትል ሰብሳቢው ገለጻ ቦርዱ ፓርቲዎቹ ላይ እርምጃውን የወሰደው በህጉ መሰረት ፓርቲዎች አሉ ስለ ተባሉት ሴት አባላት ማስረጃ ጠይቆ ማቅረብ ባለመቻላቸው ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም