ቀጥታ፡

የእግር ኳስ ኃያላኑን ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎናን ለ301ኛ ጊዜ የሚያገናኘው የኤል ክላሲኮ ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2017(ኢዜአ)፦ በስፔን ላሊጋ የ11ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና የሚያደርጉት ተጠባቂው የኤል ክላሲኮ ጨዋታ ዛሬ ይካሄዳል።

የሁለቱ ክለቦች ፍልሚያ ከምሽቱ 4 ሰዓት 85 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ሳንቲያጎ በርናባው ስታዲየም ይደረጋል።

ሪያል ማድሪድ በላሊጋው እስከ አሁን ባደረጓቸው 10 ጨዋታዎች በሰባቱ ድል ሲቀናው ሶስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ 21 ግቦችን ሲያስቆጥር 7 ጎሎችን አስተናግዷል።

በ65 ዓመቱ ጣልያናዊ ካርሎ አንቸሎቲ የሚመራው ሪያል ማድሪድ በ24 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በ59 ዓመቱ ጀርመናዊ ሃንሲ ፍሊክ የሚሰለጥነው ባርሴሎና በዘንድሮው የውድድር ዓመት በላሊጋው አስደናቂ ግስጋሴ እያደረገ ይገኛል።

ብሎግራናዎቹ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጓቸው 10 ጨዋታዎች ዘጠኝ ጊዜ ሲያሸንፉ ሽንፈት የቀመሱት አንድ ጊዜ ብቻ ነው።

በጨዋታዎቹ 33 ግቦችን ሲያስቆጥሩ 10 ግቦችን አስተናግደዋል። ባርሴሎና በ27 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።

ካርሎ አንቸሎቲ ከጨዋታው በፊት በሰጠው አስተያያት ሁለቱ ክለቦች በጠንካራ አቋም እና ራስ መተማመን ላይ የሚገኙ በመሆናቸው የጨዋታውን ውጤት ለመገመት ይከብዳል ሲል ገልጿል።

ጨዋታው በጣም አዝናኝ እንደሚሆን እጠብቃለሁ ያሉት አሰልጣኙ በደጋፊያችን ፊት የተሻለ ውጤት ለማስመዘገብ እንጫወታለን ብለዋል።

ሀንሲ ፍሊክ በበኩሉ በጨዋታው የሪያል ማድሪድ ተጫዋቾች የመጫወቻ ቦታ እንዳያገኙ እንደ ቡድን ተጭነን እንጫወታለን፣ ተጋጣሚያችን ፈጣን ተጫዋቾች ቢኖሩትም በቡድኔ ላይ ሙሉ እምነት አለኝ ሲል ተናግሯል።

ፍሊክ የቡድኑን አንድነት እና የመጫወት ተነሳሽነት ያደነቀ ሲሆን በምንከተለው የጨዋታ ስልት ጥሩ ውጤት ይዘን ለመውጣት እንጥራለን ብሏል።

የሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና ታሪካዊ ተቀናቃኝነት ከ120 ዓመታት በላይ የዘለቀ ነው።

ሁለቱ ክለቦች እ.አ.አ በ1902 ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ባርሴሎና 3 ለ 1 አሸንፏል።

ቡድኖቹ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ጨምሮ እስከ አሁን 300 ጊዜ እርስ በእርስ ተገናኝተዋል።

ባርሴሎና 125 ጊዜ ሲያሸንፍ ሪያል ማድሪድ 111 ጊዜ ድል ቀንቶታል። 64 ጊዜ አቻ ወጥተዋል።

በላሊጋው 188 ጊዜ ተገናኝተው ሪያል ማድሪድ 79 ጊዜ ሲያሸንፍ ባርሴሎና 74 ጊዜ አሸንፏል። 35 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

በ12 ግቦች የላሊጋውን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት የሚራው ፖላንዳዊው ሮበርት ሌዋንዶውስኪ እና ላሚን ያማል እና ራፊና ከባርሴሎና እንዲሁም የሪያል ማድሪድ ቪኒሺየስ ጁኒየር ኪሊያን ምባፔ እና ቤሊንግሀም በጨዋታው ላይ ልዩነት ይፈጥራሉ ተብለው የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው። 

ሪያል ማድሪድ በሳምንቱ አጋማሽ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከመመራት ተነስቶ ቦሩሲያ ዶርትሙንድን 5 ለ 2 እንዲሁም ባርሴሎና ባየር ሙኒክን 4 ለ 1 በማሸነፍ ያሳዩት ድንቅ ብቃት የዛሬውን ጨዋታ ይበልጥ ተጠባቂ አድርጎታል።

የ41 ዓመቱ ሆዜ ማሪያ ሳንቼዝ ማርቲኔዝ የሁለቱን ክለቦች ተጠባቂ ፍልሚያ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም