ቀጥታ፡

የምእራብ ጉጂ ዞን አርሶ አደሮች ከሰብል ልማት ጎን ለጎን በቅመማ ቅመም ልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለጹ

ነገሌ ቦረና፤ ጥቅምት 16/2017(ኢዜአ)፡- የምእራብ ጉጂ ዞን አርሶ አደሮች ከሰብል ልማት ጎን ለጎን በቅመማ ቅመም ልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለጹ፡፡ 

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት በበኩሉ ኮረሪማን ጨምሮ ከ580 ሄክታር በላይ መሬት በቅመማ ቅመም እየለማ መሆኑን አስታውቋል።


 

በዞኑ ቀርጫ ወረዳ የለሚ ቀርጫ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተስፋዬ ቁንቢ የኮረሪማ ልማት ጊዜ፣ ወጪና ጉልበት ቆጣቢ አምራቹንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ይላሉ፡፡

ባለፈው አመት በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት ኮረሪማ ለመጀመሪያ ጊዜ 10 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው ዘንድሮም የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ የቀርጫ ኢንሴ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገመቹ ሎሌ፣ ከቡናና ከሰብል ልማት ጎን ለጎን ከሶስት አመት ወዲህ ኮረሪማና በርበሬ ማልማት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

ባለፈው አመት ለመጀመሪያ ጊዜ ካለሙት ግማሽ ሄክታር መሬት ወደ ሁለት ኩንታል ኮረሪማ እና 12 ኩንታል በርበሬ ምርት ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት ካገኙት የኮረሪማና የበርበሬ ምርት ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተው ዘንድሮ ከ3 ኩንታል በላይ የኮረሪማ ምርት ለመሰብሰብ የምርት እንክብካቤ እያደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 

በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ኮረሪማ እያለሙ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዞኑ ቀርጫ ወረዳ የበልጎ ሚጪጫ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዱቤ ጉሚ ናቸው።

''ከልማቱም ከ8 እስከ 10 ኩንታል ምርት በመሰብሰብና ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ የመሆን እቅድ አለኝ'' ብለዋል፡፡

የዞኑ ግብርና የጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ አያኖ አለማየሁ፣ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የቅመማ ቅመም ኢኒሸቲቭ በዞኑ 6 ወረዳዎች መጀመሩን አመልክተዋል፡፡

ኢኒሸቲቩ የተጀመረው በዞኑ አባያ፣ ቀርጫ፣ ቡሌ ሆራ፣ ገላናና ከጀዋ ቢርቢርሳ ወረዳዎች በ583 ሄክታር መሬት ላይ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ 102 ሄክታር መሬት በኮረሪማ እየለማ እንደሆነ ጠቅሰው በተጨማሪም ጤና አዳም፣ ዝንጅብል፣ በሶብላ፣ ሮዝመሪ፣ አብሽ፣ ነጭና ጥቁር አዝሙድ ይገኝበታል ብለዋል፡፡

በኢኒሸቲቩ ከ1 ሺህ 90 የሚበልጡ የምእራብ ጉጂ ዞን አርሶ አደሮች በመሳተፍ ላይ እንደሆኑም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም