ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የአልዛይመር በሽታ መንስኤና መፍትሄው ምንድነው? - ኢዜአ አማርኛ
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የአልዛይመር በሽታ መንስኤና መፍትሄው ምንድነው?

የአልዛይመር በሽታ ቀስ በቀስ የአንጎል የማስታወስ ችሎታን የሚቀንስ ፤ የአስተሳሰብ፣ የቋንቋ የአመለካከትና የማስታወስ ዕክሎችን የሚያጠቃልል ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው ከ55 ሚሊዮን የሚልቁ የዓለም ህዝቦች በአልዛይመር በሽታ ተጠቂ ሲሆኑ ከእነዚህም ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ናቸው።
በየዓመቱም 10 ሚሊዮን አዳዲስ ሰዎች በበሽታው እንደሚያዙ የድርጅቱ መረጃው ያትታል።
በአሜሪካን አሪዞና የባሮው የኒዮሮሎጂካል ኢንስቲትዩት የስነ-አዕምሮና የነርቭ ፕሮፌሰር ዮናስ እንዳለ ገዳ፥ በዘርፉ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉና በርካታ የምርምር ጽሁፎችን ያሳተሙ ሲሆን፣ የአልዛይመር በሽታን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
እንደ ፕሮፌሰር ዮናስ ገለጻ፣ በዓለማችን በርካታ ሰዎች ከአልዛይመር ወይም የመርሳት በሽታ ጋር የሚታገሉ ሲሆን፣ ይህ በሽታ ከቀላል የመርሳት ደረጃ በመነሳት ሙሉ ለሙሉ እስከ መርሳት ደረጃ የሚደርስ መሆኑን ያነሳሉ።
የአልዛይመር በሽታን ለመረዳት የሰው ልጅ የአንጎል ክፍሎችን ተግባር ማወቅ ወሳኝ መሆኑን ያነሳሉ።
በዚህም፣ የግራው የአንጎል ክፍል ለቋንቋ፣ የቀኝ ለአቅጣጫ፣ የፊት ለፊቱ ለማመዛዘን እንዲሁም የኋላኛው የአንጎል ክፍል ደግሞ የሰዎችን ፊት ለመለየት የሚያገለግሉ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
በመሆኑም አልዛይመር እነዚህን የአንጎል ክፍሎች ተግባር የሚያሳልጡ ነርቮች በሂደት እንዲሞቱ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
በሂደትም የአልዛይመር በሽታ ስር እየሰደደ ሲሄድ ዲሜንሺያ(dementia) ወደተባለ ሙሉ ለሙሉ የመርሳት በሽታ የሚያድግ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የአልዛይመር በሽታ 70 በመቶ የሚሆነው ለዲሜንሺያ ወይም ሙሉ ለሙሉ የመርሳት በሽታ መንስኤ እንደሆነ አንስተዋል።
እንዲሁም 20 በመቶ የሚሆነው ደም አንጎል ውስጥ ሲፈስ የሚከሰት ሲሆን፣ የተቀረው ደግሞ በመኪና አደጋና ሌሎች ክስተቶች እንደሚፈጠር ገልጸዋል።
በሽታው ወደዚህ ደረጃ ሲያድግም፣ ግለሰቡ መደበኛ የእለት እለት ተግባሩን ለማከናወን ይሳነዋል ነው ያሉት።
በሽታው በተለይ እድሜያቸው ከፍ ያለ ሰዎች ላይ በስፋት የሚከሰት ስለመሆኑም ፕሮፌሰር ዮናስ አብራርተዋል።
በዚህም በአሜሪካን ሀገር በተደረገ ጥናት እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ያሉት እስከ 15 በመቶ የአልዛይመር በሽታ ተጠቂ መሆናቸውን አንስተዋል።
ዕድሜያቸው ከፍ እያለ ሲሄድ የተጠቂነታቸው መጠን እንደሚጨምርም የጠቆሙት ፕሮፌሰሩ፥ በኢትዮጵያም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሰዎች በዚህ በሽታ የሚጠቁ መሆኑን ገልጸዋል።
ነገር ግን ቁጥራቸው ምን ያክል እንደሆነ ጥርት ያለ መረጃ ባለመኖሩ በዚሁ ዙሪያ በቂ ጥናት ለማድረግ ከተለያዩ የምርምር ተቋማትና ዩኒቨርሲዎች ጋር በመሆን እንቅስቃሴ መጀመራቸውንተናግረዋል።
ይህ የአልዛይመር ወይም የመርሳት በሽታ ከጅምሩ አንስቶ ቀስ በቀስ ወደ ዲሜንሺያ ደረጃ ወይም ሙሉ በሙሉ ወደ መርሳት ከመድረሱ በፊት በቀላሉ ማከም እንደሚቻልም ጥናታቸውን በዋቢነት ጠቅሰዋል።
ይህም በአሜሪካን ሀገር ለአምስት ዓመታት በ2 ሺህ የበሽታው ተጠቂዎች ላይ ባደረጉት ጥናት ቀለል ያለ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በሽታውን የሚቀንስ እና የሚከላከል እንደሆነ መረጋገጡን ገልጸዋል።
በተጨማሪም እንደ የሙዚቃ መሳሪያ መጫወት፣ እጅ ሥራ (ለምሳሌ ኪሮሽ መስራት)፣ ኮምፒዩተር መጠቀም እንዲሁም ጤናማ የሆነ የአመጋገብ ስልት በመከተል በሽታውን መቀነስ እንደሚቻል አረጋግጠዋል።