ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ዩኒሴፍ በአየር ንብረት ለውጥ እና በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር ለማጎልበት እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ።

29ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 29) የተመለከተ የአየር ንብረት ሳምንት ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ ተደርጓል።

የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ከአየር ንብረት ሳምንት ጎን ለጎን የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) የኢትዮጵያ ተወካይ አቡበከር ካምፖ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒስትሯ ዩኒሴፍ ከኢትዮጵያ ጋር በሕጻናት ክብካቤ ማዕከላት ማቋቋም፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ሌሎች መስኮች በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በያዘችው የሪፎርም አጀንዳ ከሁሉም የልማት አጋሮች ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር እንደምትሰራ አመልክተዋል።

የልማት አጋሮች የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለውጥ በማዕቀፎቻቸው ውስጥ ለማካተት ያላቸውን ሀሳብ አድንቀዋል።

የአጋሮች የልማት እና የፋይናንስ የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲ እና ትግበራ ለማሳካት ወሳኝ ናቸው ብለዋል ሚኒስትሯ።

የብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ እቅድ (NDC) እና የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ የካርበን ልቀት ስትራቴጂ (LT-LEDS) የዚሁ ስራ አካል መሆናቸውን አስረድተዋል።

ሁሉም ባለድርሻ አካላት የኢትዮጵያ አረንጓዴ እድገት እና ዘላቂ እድገት እንዲሁም በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፎች ውስጥ ያላት ሚና እንዲያድግ የሚያስችሉትን ፖሊሲዎች እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይ አቡበከር ካምፖ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን አየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲ አድንቀው ችግሩን ለመከላከል እየወሰደች ያለው እርምጃ ለተቀረው ዓለም ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።

ዩኒሴፍ ድህነትን ለመከላከል ስትራቴጂካዊ የሆነ የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችለውን ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በውይይቱ ኢትዮጵያ እና ዩኒሴፍ የጀመሩትን ምክክር በአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔውም በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ ለመቀጠል ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ሁለቱ ወገኖች ከአየር ንብረት ለውጥ ባለፈ በሌሎችም መስኮች ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም