ቀጥታ፡

በድሬዳዋ የወባ በሽታን ለመከላከል የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ተመለከተ

ድሬዳዋ፤ ጥቅምት 15/2017(ኢዜአ)፡- በድሬዳዋ እየተስፋፋ የሚገኘውን የወባ በሽታ ለመከላከል የተጀመሩ ተግባራትን ለማጠናከር ተቀናጅቶ መረባረብ እንደሚገባ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ አስገነዘቡ።

በድሬዳዋ ሀገር አቀፍ የወባ ሳምንትን ምክንያት በማድረግ ወባን ለመከላከልና ህሙማንን ለማዳን እየተሰሩ በሚገኙ ተግባራት ላይ ውይይት ተካሂዷል።

ውይይቱን የመሩት የጤና ቢሮ ኃላፊዋ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ እንደተናገሩት፤ በገጠርና በከተማ ባለፉት ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ መንገድ የወባ ወረርሽኝ ተከስቶ የተቀናጀ የመከላከል ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ቢጨምርም የጤና ተቋማት ባለሙያዎች በበሽታው የተያዘ አንድም ሰው ህይወቱ እንዳያልፍ ውጤታማ ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

የክረምት ወራት የፈጠረው ጫና፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ እንዲሁም ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በአግባቡ አለማፅዳትን በምክንያትነት አንስተዋል።

በተጨማሪም ህብረተሰቡ ለወባ ትንኝ መከላከያ የታደለውን ኬሚካል የተነከረ አጎበር በአግባቡ አለመጠቀሙ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ችግሩን በተቀናጀ መንገድ መከላከል የሚያስችል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የወባ መራቢያ ናቸው ተብለው በተለዩ አካባቢዎች ላይ ፀረ ትንኝ ኬሚካል ርጭት ተጀምሯል።

በህዝብ ንቅናቄ እና በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በቤት ለቤት እና በብሎክ አደረጃጀት ግንዛቤ የመፍጠርና በትንኝ የተበከሉ የውሃ ማጠራቀሚያዎችን የማፅዳት ስራ እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።

በመሆኑም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና የጤና ባለሙያዎች የተጀመረውን አበረታች የመከላከል ዘመቻ በተቀናጀ መንገድ በመተግበር ከወባ ነፃ የሆነች ድሬዳዋን እውን ለማድረግ መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ የወባ እና የተላላፊ በሽታዎች መከላከል ባለሙያ አቶ አለማየሁ ቁልጬ በበኩላቸው በድሬዳዋ ከተማና ገጠር ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ የወባ ወረርሽኝ መከሰቱን ገልጸዋል።

ወባን በተቀናጀ ህዝባዊ ንቅናቄ ለመከላከል የተጀመሩና ለውጥ የመጣባቸው አበረታች የመከላከልና ህሙማንን የማዳን ተግባራትን በማጠናከር የተሻለ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አመልክተዋል።

በመልካጀብዱ፣ በቡቲጂ ወንዝ እና በገንደ ገራዳ በተባሉ ዋነኛ የወባ መራቢያ አካባቢዎች እና የመኖሪያ ቤቶች ላይ የተጀመረው የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭትን በማስቀጠል የተሻለ ውጤት ለማምጣት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በውይይቱ የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማና ገጠር ወረዳዎች የጤና ተቋማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የወረዳ አመራሮችና እና የማህበረሰብ ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም