ቀጥታ፡

በጉባዔው የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለውጥ ግቦች የሚያሳኩ ዓለም አቀፍ አጋርነቶችን የማጠናከር ስራ በትኩረት ይከናወናል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ግቦቿን እውን የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ አጋርነቶችን የማጠናከር ስራ በ29ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ(ኮፕ29) እንደምታከናውን የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኮፕ29 ከሕዳር 2 እስከ 13 ቀን 2017 ዓ.ም በአዘርባጃን ባኩ ከተማ ይካሄዳል።

ኢትዮጵያ በጉባዔው ላይ የሚኖራትን ተሳትፎ አስመልክቶ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እና ግንዛቤ ማሳደግን አላማ ያደረገ የብዙሃን መገናኛ አመራሮች እና ባለሙያዎች የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።


 

የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የአካባቢ እና አየር ንብረት ለውጥ ስምምነትና አጋርነት ከፍተኛ ባለሙያ መንግስቱ በሾ ኢትዮጵያ በኮፕ 29 የሚኖራትን ተሳትፎ አስመልክቶ የድርጊት መርሃ ግብር መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የጉባዔውን ተሳትፎ የሚያስተባብር ብሔራዊ የስትሪንግ ኮሚቴ እና በኮሚቴው ስር የተለያዩ የቴክኒክ ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን ፍላጎቶች እና ጥቅሞች የሚያስከብሩ 20 የጎንዮሽ እና 40 የሁለትዮሽ ውይይቶችን ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።

ከጉባዔው ጎን ለጎን የሀገራት መሪዎች እና ሚኒስትሮች የሚሳተፉባቸው የተለያዩ መድረኮች እንደሚካሄዱም ነው የጠቆሙት።

በኮፕ29 የኢትዮጵያ ድንኳን(Ethiopia COP 29 Pavilion) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እያከናወነች ያለውን ስራ እንደሚቀርብ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በጉባዔው ሶስት የአጋርነት ስምምነቶችን እንደምትፈራረም በመጠቆም።

አረንጓዴ አሻራ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ግብ፣ የብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ እቅዶች ትግበራ እና በአየር ንብረት ለውጥ ለሚደርስ ጉዳት እና ኪሳራ የሚከፈል የፋይናንስ ፈንድ ማዕቀፍ ኢትዮጵያ ትኩረት ከሰጠቻቸው ጉዳዮች በዋናት እንደሚጠቀሱ አመልክተዋል።

የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን፣ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ ግብን ጨምሮ ሌሎች ያልተቋጩ ጉዳዮች እንዲፈቱ ድምጿን እንደምታሰማም ነው የተናገሩት።

የአየር ንብረት ለውጥ ገፈት ቀማሾች የሆኑት የአፍሪካ እና በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት የጋራ አቋም በመያዝ ግፊት እንዲያደርጉ ጥረት ታደርጋለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ በጉባዔው ጥቅሞቿን ለማስከበር የተቀናጀ የዲፕሎማሲ ስራ ይከናወናል ነው ያሉት።

ዴንማርክ፣ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም(ዩኤንዲፒ)፣ የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት(ዩኒሴፍ)፣ የዓለም ባንክ፣ ዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ(ኢፋድ) እና ሌሎች አጋር አካላት ለኢትዮጵያ የኮፕ29 ተሳትፎ ድጋፍ እንዳደረጉም ጠቁመዋል።

የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲ ዳይሬክተር ስምረት ተረፈ በበኩላቸው በጉባዔው ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ግቧቿ እና የብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ እቅዶቿ ትግበራ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ለማግኘት ጥረት እንደሚደርግ አመልክተዋል።

የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥ ፕሮግራም አማካሪ መድህን ፍስሐ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ በኮፕ 29 የምታቀርባቸውን አጀንዳዎች በማጉላት ፍላጎቷን እና ጥቅሟን እንድታሳካ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በውይይቱ ላይ በኮፕ 29 የኢትዮጵያ ተሳትፎ ላይ መገናኛ ብዙሃን፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ወጣቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሚናን የተመለከቱ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በፕላን እና ልማት ሚኒስቴር አስተባባሪነት በኮፕ 29 ተሳትፎ ለማድረግ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም