ትውልዱን የሚያንፁ የሥነ-ምግባር ግንባታ ሥራዎችን በሚዲያ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል - ሣሙኤል ኡርቃቶ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ትውልዱን የሚያንፁ የሥነ-ምግባር ግንባታ ሥራዎችን በሚዲያ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል - ሣሙኤል ኡርቃቶ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2017(ኢዜአ)፦ትውልዱን የሚያንፁ የሥነ-ምግባር ግንባታ ሥራዎችን በሚዲያ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሣሙኤል ኡርቃቶ(ዶ/ር) ገለፁ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በፀረ-ሙስና ትግሉ ላይ በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራርመዋል።
የመግባቢያ ሥምምነቱን የፌዴራል ሥነ- ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሣሙኤል ኡርቃቶ(ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ተፈራርመዋል፡፡
ኮሚሽነር ሣሙኤል ኡርቃቶ(ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ፤ የፀረ-ሙስና ትግሉና ትውልድን በስነ-ምግባር የማነጽ ተግባሩ ያለመረጃ ተደራሽነት ውጤታማ እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ስምምነቱ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለኅብረተሰቡ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ እንዲደርስ ከኢዜአ ጋር መሥራት ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም የኢዜአ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስን በመጠቀም ትውልድን የሚያንፁ የሥነ-ምግባር ግንባታ ሥራዎችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው ሁለቱ ተቋማት በጋራ መሥራታቸው ተቋማዊ ተልዕኳቸውን ለማሳካት ያግዛቸዋል ብለዋል።
በተለይም ብሔራዊ ጥቅምን ከማስከበር አኳያ ሁለቱ ተቋማት ተቀራርበው ውጤታማ ስራ ማከናወን እንደሚችሉ አብራርተዋል፡፡
ኢዜአ ለፀረ-ሙስና ትግሉ ውጤታማነት በዲጂታል ዘዴዎች የመረጃ ስብጥሩን በማስፋትና አጀንዳ በመቅረፅ ሕዝቡ ውስጥ የማስረፅ ተልዕኮውን በብቃት ለመፈፀም እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
ኢዜአ በኢትዮጵያ 38 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፤ በአምስት የሀገር ውስጥና በሶስት የውጭ ቋንቋዎች ለሀገር ወስጥና ለውጭ ዜጎች ዜናና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል።