ቀጥታ፡

በዘንድሮው የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ አጀንዳዎች ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎችን ያማከሉ ሊሆኑ እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2017(ኢዜአ)፦ በዘንድሮው የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ(ኮፕ 29) አጀንዳዎች ሕጻናትና ወጣቶችን ጨምሮ ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎችን ያማከለ መሆን እንደሚገባው ተገለጸ።

29ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ(ኮፕ 29) በአዘርባጃን ባኩ ከሕዳር 2 እስከ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከመንግሥታቱ ድርጅት የሕፃናት አድን ድርጅት(ዩኒሴፍ) ጋር በመተባበር የአየር ንብረት ለውጥ ሳምንትን ይፋ ማድረጊያና የቅድመ ጉባዔ የባለድርሻ አካላት መድረክ አካሂዷል።


 

በመድረኩ "የኢትዮጵያ ልጆች እየተባባሰ በመጣ የአየር ንብረት ለውጥ ውስጥ" በሚል ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆን ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በመድረኩ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሠፋ(ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ አቡቦኩር ካምፖ(ዶ/ር)ን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሠፋ(ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መግታትና መቋቋም የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን እያከናወነች ነው።

በአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲ ማዕቀፏ ሕፃናትን ጨምሮ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያማከሉ እንዲሆኑ አበክራ እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር የሕፃናት ቀውስ በሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ህፃናት ተኮር የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲ ትግበራና ኢንቨስትመንት ላይ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ጎን ለጎንም ሕዳር ላይ በአዘርባጃን ለሚካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ(ኮፕ 29) ከራሷ አጀንዳዎች ባሻገር የአፍሪካ ድምፅ ሆና አጀንዳዎችን እንደምታስተጋባ ጠቁመዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ አትዮጵያ በዓለም አቀፍ ግዴታዋን ለመወጣት አስፈላጊ ለአየር ንብረት የማይበገሩ የኢኮኖሚ ዕድገት እርምጃዎችን እየተገበረች መሆኑን ገልፀዋል።

ሚኒስቴሩ የኮፕ 29 የድርጊት መርኃ ግብር ማዘጋጀቱንና በጉባኤው ኢትዮጵያ የራሷ ማሳያ እንደሚኖራት ጠቁመዋል።

ዛሬ ይፋ የሆነው የአየር ንብረት ሳምንትም ለጉባኤው የሚበጁ ኃሳቦች የሚንሸራሸሩበት መሆኑን ጠቁመዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ሳምንትም ሁሉን አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃን የተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫና የፖሊሲ ግብዓት ይሰበሰብበታል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ አቡቦኩር ካምፖ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽዕኖው እየበረታ በተለይም በመጠጥ ውኃ፣ በትምህርትና በምግብ አቅርቦት ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖው በተለይም ሕፃናት እንዳይጎዱ መንግሥት፣ የረጂ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የባለድርሻ አካላት ሊተባበሩ እንደሚገባ በመጠቆም።

በሚሊዮኖች የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ዩኒሴፍም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን እየተገበረ ነው ብለዋል።

በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አጀንዳዎችን የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ አጀንዳን ጨምሮ የኮፕ 29 አጀንዳዎች ሴቶችና ሕፃናትን ያማከሉ መሆን እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ የሰጠችውን ትኩረት አድንቀው፤ ከአየር ንብረት ለውጥ የተስማማ የሕፃናት ተኮር ፕሮግራም ትግበራ ዩኒሴፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሰኒ ሮግስትሩፕ ሀገራቸው ለዓለም አየር ንብረት ለውጥ ትግል ብርቱ ደጋፊ መሆኗን አስታውሰው፤ ለዚህ ዕውን መሆን የባለድርሻ አካላት ሁሉን አቀፍ ትብብር ይሻል ብለዋል።

በዘንድሮው 29ኛው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ቃል የተገባው ፋይናንስ ድጋፍ ተግባራዊ መሆን እንደሚገባው እንዲሁም የጉዳትና ካሳ አጀንዳ ቀዳሚ ትኩረት እንዲሰጠው ዴንማርክ ትደግፋለች ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የአዘርባጃን አምባሳደር ሩስላን ናሲቦቭ በባኩ በሚደረገው ጉባዔ የተሻለ ነገ ለመገንባት አዳዲስ የመፍትሄ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት እና ድርድሮች ወደ ስምምነት የሚለወጡበት እንደሚሆን ገልጸዋል።

በእስከዛሬ የኮፕ ጉባኤ ትኩረት ያልተሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ይበልጥ ትኩረት እንደሚደረግ ጠቁመው፤ በተለይም ችግሩን ለመከላከል ሰብዓዊ ልማት ዐቢይ ትኩረት መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም