የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚጸናውና የሚበየነው በመከላከያ ሰራዊት የማይበገር አገራዊ ፍቅር፣ ጀግንነትና መስዋዕትነት ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚጸናውና የሚበየነው በመከላከያ ሰራዊት የማይበገር አገራዊ ፍቅር፣ ጀግንነትና መስዋዕትነት ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 15/2017 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት የሚጸናውና የሚበየነው በመከላከያ ሰራዊት የማይበገር አገራዊ ፍቅር፣ ጀግንነትና መስዋዕትነት ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
117ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን "በፈተናዎች እየተገነባ የመጣ ሠራዊት" በሚል መሪ ኃሳብ በመከላከያ ሰራዊት ዋና መምሪያ በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።
በመርኃ ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፣ የሰራዊቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና አባላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር ሰላም፣ ደኅንነትና ሉዓላዊነት በደሙ ያጸና ነው።
ኢትዮጵያም በዚህ መስዋዕትነት ጸንታ ቆማለች ያሉት ፕሬዝዳንቱ ለዚህም ሠራዊቱን ማመስገን ይገባል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያን ከየትኛውም አቅጣጫ ለመጠበቅ ከምንግዜውም በላይ በከፍተኛ ብቃትና ዝግጁነት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ 117 ዓመታትን ያስቆጠረው ዘመናዊ የመከላከያ ሰራዊት ተቋም ባለቤት መሆኗ የሚያኮራና የኢትዮጵያዊያንን ብርታትና ጽናት ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የአገራችን አንድነትና የፖለቲካ ነጻነት የሚጸናውና የሚበየነው በመከላከያ ሰራዊት የማይበገር አገራዊ ፍቅር፣ ጀግንነትና መስዋዕትነት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በመከላከያ ሠራዊት የተሰራው የሪፎርም ሥራ ከሀገር አልፎ በአፍሪካ በተምሳሌትነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ ጽኑ መሠረት መሆኑን ተናግረው፤ ለሁለንተናዊ እድገት መረጋገጥ ከጀግናው ሰራዊት ጋር መቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ታሪካዊ ጠላቶች በቀጥታ ካደረጉት ውጊያ በተጨማሪ ባንዳዎችን በመላክ ኢትዮጵያን ሲያዳክሙ መቆየታቸውን አንስተዋል።
ብዙ ነጻ አውጭዎች ነን ባዮችን በመፈልፈልና በማሰልጠን ሰላም ሲነሱ መኖራቸውን ጠቅሰው ያም ሆኖ አልተሳካላቸውም ነው ያሉት።
አሁንም ደካማ አገር ለመፍጠር በተላላኪዎቻቸው በኩል ይህንን ሴራ አጠናክረው መቀጠላቸውን አንስተው ለዚህም ዋነኛ ምክንያት አገሪቱ ልማቷን እያጠናከረች መሆኑን ነው ያነሱት።
ሰራዊቱ ኢትዮጵያ ልማቷን እንዳታፋጥንና ብሔራዊ ጥቅሟን እንዳታገኝ እየሰሩ ያሉ ባንዳዎችን እየቀጣና የጀመረችውን የልማት ውጥን እንድታሳካ አገራዊ ኃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሰራዊቱ በዘመናዊ ትጥቅ የተደራጀና በሰለጠነ የሰው ኃይል የተገነባ መሆኑን ጠቅሰው የትኛውንም አይነት ግዳጅ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አመላክተዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት የአገሪቱን እድገት ማዕከል ያደረገ ቁመና ላይ መሆኑን ያነሱት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሰራዊቱ ለአገር ሉዓላዊነትና ለኢትዮጵያ ሰላም ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለሀገር ከመቆም በላይ ክብር የለም ያሉት ደግሞ የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ናቸው።
ዕለቱ ለሰራዊቱ ፍጹም ጀግንነትና ቆራጥነት እውቅና ከመስጠት ባሻገር የወትሮው ዝግጁነቱን የሚያጠናክርበት መሆኑን ገልጸዋል።
በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮች ሰራዊቱን የሚያዳክሙ ሳይሆን ወደ ታላቅነት የሚወስዱት መሆኑን አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በፈተናዎች ሁሉ ያለፈ ቁርጠኛ ሰራዊት መሆኑን ገልጸው፤ አሁንም ይበልጥ አይበገሬነቱን እያስመሰከረ መሆኑን ተናግረዋል።
እንዲሁም የጥንካሬ ተምሳሌት ሆኖ መቀጠሉን ገልጸው፤ በመከላከያ የተደረገው ሪፎርም ሰራዊቱን በውጤታማነት ወደፊት ማሸጋገሩን አንስተዋል።
አመርቂ ድሎችን በማስመዝገብ ነገን የሚሻገር መሰረት መጣሉንና የሰራዊቱ ጥንካሬ የኢትዮጵያ ጥንካሬ መሆኑን ሚኒስትሯ አያይዘው ገልጸዋል።