የማሌዥያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚፈልጉ አስታወቁ - ኢዜአ አማርኛ
የማሌዥያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚፈልጉ አስታወቁ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 15/2017 (ኢዜአ)፡- የማሌዥያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በመሳተፍ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል፡፡
ወደ ማሌዥያ ለሥራ ጉብኝት ያቀናው የኢትዮጵያ ልዑክ በሀገሪቱ ከሚገኙ የቢዝነስ ማሕበረሰብ አባላት ጋር መክሯል፡፡
በዚሁ ወቅትም በኢትዮጵያ ስለሚገኙ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የልዑካን ቡድኑ አባላት አብራርተዋል፡፡
በተለይም በማኑፋክቸሪንግ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በፋርማሲዩቲካል፣ በቴክስታይልና ጋርመንት፣ በማዕድንና ኮንስትራክሽን ዘርፎች ላይ የማሌዥያ ባለሃብቶች እንዲሠማሩ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በሀገራቱ መካከል ጠንካራ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲኖር፣ ኢትዮጵያ ስላላት የኢንቨስትመንት እድልና ቅድሚያ ስለሚሰጣቸው ዘርፎች እና ለባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ምኅዳር ለመፍጠር የተከናወኑ የሪፎርም ተግባራት ገለፃ ተደርጓል፡፡
የማሌዥያ ቢዝነስ ማሕበረሰብ አባላት በበኩላቸው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት የሚያደርግ ልዑክ እንልካለን ማለታቸውን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት ልውውጥም ለማሳደግ እንደሚሠሩ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።