በዘመናዊ ትጥቅና በሰለጠነ የሰው ኃይል የተደራጀው መከላከያ ሠራዊት አገር የመጠበቅ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2017(ኢዜአ)፦ በዘመናዊ ትጥቅና በሰለጠነ የሰው ኃይል የተደራጀው መከላከያ ሠራዊት አገር የመጠበቅ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

117ኛው የመከላከያ ሰራዊት ቀን በመከላከያ ሰራዊት ዋና መምሪያ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ነው።


 

በመርኃ ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ የሰራዊቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና አባላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ዕለቱን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጎን ለጎንም ታሪካዊ ጠላቶች በቀጥታ ካደረጉት ውጊያ በተጨማሪ ባንዳዎችን በመላክ ኢትዮጵያን ሲያዳክሙ መቆየታቸውን አንስተዋል።

ብዙ ነጻ አውጪዎች ነን ባዮችን በመፈልፈልና በማሰልጠን ሰላም ሲነሱ መኖራቸውን ጠቅሰው ያም ሆኖ አልተሳካለቸውም ነው ያሉት።

አሁንም ደካማ አገር ለመፍጠር በተላላኪዎቻቸው በኩል ይህንን ሴራ አጠናክረው መቀጠላቸውን አንስተው ለዚህም ዋነኛ ምክንያት አገሪቱ ልማቷን እያጠናከረች መሆኑን ነው ያነሱት።

ሰራዊቱ ኢትዮጵያ ልማቷን እንዳታፋጥንና ብሔራዊ ጥቅሟን እንዳታገኝ እየሰሩ ያሉ ባንዳዎችን እየቀጣና የጀመረችውን የልማት ውጥን እንድታሳካ አገራዊ ኃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሰራዊቱ በዘመናዊ ትጥቅ የተደራጀና በሰለጠነ የሰው ኃይል የተገነባ መሆኑን ጠቅሰው የትኛውንም አይነት ግዳጅ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አመላክተዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት የአገሪቱን እድገት ማዕከል ያደረገ ቁመና ላይ መሆኑን ያነሱት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሰራዊቱ ለአገር ሉዓላዊነትና ለኢትዮጵያ ሰላም ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

በመርኃ ግብሩ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በተለያዩ መንገዶች ሰራዊቱን ሲደግፉና የሚሰነዝሩ ትችቶችን ሲመክቱ ለነበሩ አራት ግለሰቦች የመከላከያ ሰራዊት የክብር አባልነት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም