የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያ ጽኑ መሠረት ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያ ጽኑ መሠረት ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 15/2017 (ኢዜአ)፦ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያ ጽኑ መሠረት ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ተናገሩ።
117 ኛው የመከላከያ ሰራዊት ቀን "በፈተናዎች እየተገነባ የመጣ ሠራዊት" በሚል መሪ ሀሳብ በመከላከያ ሰራዊት ዋና መምሪያ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ነው።
በመርሀግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ፣ የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሀመድ ፣ የሰራዊቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና አባላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሀገር ሰላም፣ ደህንነት እና ሉአላዊነት በደሙ ያጸና መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያም በዚህ መስዋዕትነት ጸንታ ቆማለች ያሉት ፕሬዝዳንቱ ለዚህም ሰራዊቱን ማመስገን ይገባል ነው ያሉት።
መከላከያ ሰራዊት ላይ የተሰራው የሪፎርም ስራ ከሀገር አልፎ በአፍሪካ በተምሳሌትነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።
ለዚህም በቅርቡ በአዲስ አበባ የተገኙት የአፍሪካ አገራት መከላከያ ሚኒስትሮች ምስክርነት የሰጡበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያ ጽኑ መሠረት መሆኑን ተናግረው፤ ለሁለንተናዊ እድገት መረጋገጥ ከጀግናው ሰራዊት ጋር መቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።