ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከብሪክስ አባል አገራት መሪዎች ጋር በነበራቸው ውይይት የኢትዮጵያን ሰጥቶ በመቀበል መርህ የባህር በር የማግኘት ፍላጎት አንጸባርቀዋል - ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2017(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከብሪክስ አባል አገራት መሪዎች ጋር በነበራቸው የሁለትዮሽ ውይይት የኢትዮጵያን በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር የማግኘት ፍላጎትንና አቋም ማንጸባረቃቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

16ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ በሩሲያ ካዛን ከተማ መካሄዱ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሚኒስትሮች ልዑካን ቡድን ጋር በመሆን በጉባዔው ላይ ተሳትፈዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በጉባዔው የነበራትን ተሳትፎ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባዔው ላይ፣ በሁለትዮሽ እና በባለብዝሃ ወገን የምክክር መድረኮች ላይ ውጤታማ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባዔው ላይ አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ማግኘት እንዳለባት እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓቱ አካተች እንዲሆን ያቀረቡት ጥሪ ጉባዔው ተቀብሎ የጋራ አቋም እንደያዘበትም አብራርተዋል።

ከጉባዔው ጎን ለጎን ከብሪክስ አባል እና አጋር አገራት መሪዎች ጋር በተደረጉ የሁለትዮሽ ውይይቶች የኢትዮጵያን አቋሞች ማንጸባረቅ እንደተቻለም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከወደብ አኳያ ኢትዮጵያ ከታሪክም፣ የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የሕዝብ ብዛት እና የኢኮኖሚ እድገቷን የሚመጥን የባህር በር ማግኘት እንደሚገባት ከአገራት መሪዎች ጋር በነበራቸው ውይይቶች ላይ ማንሳታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄዋን የሰጥቶ መቀበል መርህን መሰረት ያደረገ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቶቻቸው በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓቱ ማሻሻያ እንዲደረግ ያቀረቡት ሀሳብ በሌሎች አገራትም ተቀባይነት ማግኘቱንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በመድረኩ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና ተቋማት ግንባታን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች እያደረች የምትገኛቸውን ማሻሻያዎች አስመልክቶም ለአገራት መሪዎች ገለጻ መደረጉንም ነው ሚኒስትሩ ያብራሩት።

የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ኢትዮጵያ ከታሰበው በላይ በኢኮኖሚ፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና የተለያዩ መስኮች ተጠቃሚ መሆን እንደምትችል ግንዛቤ የተወሰደበት እንደሆነም ተናግረዋል።

በብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ላይ የተላለፉ ውሳኔዎች እና የተያዙ የጋራ አቋሞች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች እና ፍላጎቶች የሚያሳኩ ሆነው መገኘታቸውንም ነው ሚኒስትሩ ያመለከቱት።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በጉባዔው ላይ ስኬታማ ተሳትፎ ማድረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም