ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ተግባራዊ ያደረገችው ፖሊሲ ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች ያማከለ እንዲሆን ትኩረት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ አየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ተግባራዊ ያደረገቸው ፖሊሲ ሕፃናትን ጨምሮ ለተፅዕኖው ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያማከለ እንዲሆን ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሠፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

ፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከመንግሥታቱ ድርጅት የሕፃናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ጋር በመተባበር  የአየር ንብረት ለውጥ ሳምንትን ይፋ ማድረጊያና በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው። 

በመድረኩ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሠፋ (ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ አቡቦኩር ካምፖ(ዶ/ር)ን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተግኝተዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሠፋ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመግታትና ተፅዕኖ ለመቋቋም የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን እያከናወነች ነው።

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲ ማዕቀፏ ሕፃናትን ጨምሮ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያማከሉ እንዲሆኑ አበክራ እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ ፖሊሲ ማዕቀፍም ሕፃናት ተኮርና ንፁህ፣ ጤናማና ዘላቂ ከባቢ የማግኘት መብቶችን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዩኔሴፍ ጋር በመተባበር የሕፃናት ቀውስ በሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ህፃናት ተኮር የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲ ትግበራና ኢንቨስትመንት ላይ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ጎን ለጎንም ሕዳር ላይ በአዘርባጃን ለሚካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ(ኮፕ 29) ከራሷ አጀንዳዎች ባሻገር የአፍሪካ ድምፅ ሆኖ አጀንዳዎችን እንደምታስተጋባ ጠቁመዋል። 

በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ አትዮጵያ በዓለም አቀፍ ግዴታዋን ለመወጣት አስፈላጊ ለአየር ንብረት የማይበገሩ የኢኮኖሚ ዕድገት እርምጃዎችን እየተገበረች መሆኑን ገልፀዋል። 

ሚኒስቴሩ የኮፖ_29 የድርጊት መርኃ ግብር ማዘጋጀቹንና በጉባኤው ኢትዮጵያ የራሷን ማሳያ (ፓቪሎን) እንደሚኖራት ገልፀዋል። 

ዛሬ ይፋ የሆነው የአየር ንብረት ሳምንትም ለጉባኤው የሚበጁ ኃሳቦችን የሚንሸራሸሩበት መሆኑን ጠቁመዋል። 

የአየር ንብረት ለውጥ ሳምንትም የሁሉን አቀፍ የአየር  ንብረት ለውጥ እርምጃን የተመላከተ የግንዛቤ ማስጨበጫና የፖሊሲ ግብዓት ይሰበሰብበታል ነው ያሉት። 

በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ አቡቦኩር ካምፖ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አየርን ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽዕኖው እየበረታ መጥቷል።

ይህም በተለይም በመጠጥ ውኃ፣ በትምህርትና ምግብ አቅርቦት ጫና እያሳደረ መሆኑን ነው የገለጹት።

ያም ብቻ ሳይሆን የአየር ንብረት ለውጥ በሌሎች መስኮች ላይም አሉታዊ ተፅኖው ከባድ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም የአየር ንብረት ተጽዕኖው በተለይም ሕፃናት እንዳይጎዱ በትብብር መሥራት አለብን ነው ያሉት።

በዚህም መንግሥት፣ የረጂ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የባለድርሻ አካላት ሊተባበሩ እንደሚገባ በመጠቆም። 

በሚሊዮኖች የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ዩኒሴፍም አየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የሚያስችል ፕሮጀክቶችን እየተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የሚሰሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየደገፈ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዓለም አቀፉ አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አጀንዳዎችን የአየርን ንብረት ለውጥ ፋይናንስ አጀንዳን ጨምሮ የኮፕ 29 አጀንዳዎች ሕፃናትን ያማከሉ መሆን እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ መንግሥት ለአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ የሰጠውን ትኩረት አድንቀዋል። 

ዩኒሴፍም ከአየር ንብረት ለውጥ የተስማማ የሕፃናት ተኮር ፕሮግራም በኢትዮጵያ እንዲተገበር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በመድረኩ "የኢትዮጵያ ልጆች እየተባባሰ በመጣ የአየር ንብረት ለውጥ ውስጥ" በሚል ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆን ጥናት ይቀርባል ተብሏል።

የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ ያለበትን ሁኔታ የተመለከተ በዩኔሴፍ የተጠና ጥናትም ውይይት እንደሚደረግበትም ተገልጿል።  

በውይይት በአዘርባጃን የሚካሄደውን 29ኛው የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ_29) የኢትዮጵያ ትኩረት አጀንዳዎችና የሚጠበቁ ውጤቶችን በመድረኩ ላይ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግባቸውም ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም