በብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር እና ተደማጭነትን ለመጨመር የሚያስችሉ የዲፕሎማሲ ስራዎች ተከናውነዋል- ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር እና ተደማጭነትን ለመጨመር የሚያስችሉ የዲፕሎማሲ ስራዎች ተከናውነዋል- ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2017 (ኢዜአ)፦ በብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር እና ተደማጭነትን ለመጨመር የሚያስችሉ የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ ስራዎች መከናወናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
16ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ በሩሲያ ካዛን ከተማ ተካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሚኒስትሮች ልዑካን ቡድን ጋር በመሆን በጉባዔው ላይ ተሳትፈዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በጊባዔው የነበራትን ተሳትፎ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በጉባዔው ሰፋ ባሉ አጀንዳዎች ላይ ውይይት መካሄዱንና የኢትዮጵያ ልዑክ በጉባዔው ላይ ውጤታማ ተሳትፎ ማድረጉን ገልጸዋል።
በብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር፣ ተሰሚነት እና ተደማጭነትን ለመጨመር የሚያስችሉ በርካታ የዲፕሎማሲ ስራዎች መከናወናቸውንም አመልክተዋል።
በጉባዔው በኢኮኖሚው ያሉ ትብብሮች፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያን የተመለከቱ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በውሳኔዎቹ ላይ የራሷን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን የጋራ አቋም ማንጸባረቅ መቻሏንም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።
በጉባዔው ከብሪክስ አባል አገራት በተጨማሪ ከብሪክስ ጋር በአጋርነት መስራት የሚፈልጉ አገራት መሳተፋቸውን አንስተዋል።
ከጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ አገራት ጋር ውጤታማ የሁለትዮሽ ውይይቶች መከናወናቸውን አመልክተዋል።
በተለይም የተለያዩ የብሪክስ አጋር አገራት አባል ለመሆን የኢትዮጵያን ድጋፍ መጠየቃቸውንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።
በሁለትዮሽ ውይይቶቹ አገራቱ ኢትዮጵያ በቀጣናው እና በአፍሪካ ያላትን አቋም እንዲሁም መሰረታዊ ጥቅሞቿን በተመለከተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መደረጉን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሩሲያው ፕሬዝዳን ቭላድሚር ፑቲን ስላደረጉት ውይይትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሀሳብ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ለረጅም ጊዜ የቆየ ታሪካዊ ትብብር እንዳላቸው እና በተለያዩ መስኮች የተፈራረሟቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶች እንዳሉ አንስተዋል።
ሁለቱ መሪዎች በውይይታቸው ሁለቱ አገራት ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በውይይቱ ሀገራቱ በቀጣይ በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይም አቅጣጫ መቀመጡንና የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም አክለዋል።