ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በፈተናዎች ሁሉ በማለፍ የጥንካሬ ተምሳሌት መሆኑን ቀጥሏል - ኢንጅነር አይሻ መሀመድ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በፈተናዎች ሁሉ በማለፍ የጥንካሬ ተምሳሌት መሆኑን ቀጥሏል  ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሀመድ ገለጹ።

117 ኛው የመከላከያ ሰራዊት ቀን "በፈተናዎች እየተገነባ የመጣ ሠራዊት" በሚል መሪ ሀሳብ በመከላከያ ሰራዊት ዋና መምሪያ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ነው።


 

በመርሀ ግብሩ ላይ የኢፌድሪ ፕሬዝደንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ የሰራዊቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እና አባላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሀመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ለሀገር ከመቆም በላይ ክብር የለም ብለዋል።

እለቱ ለሰራዊቱ ፍጹም ጀግንነትና ቆራጥነት እውቅና ከመስጠት ባሻገር የወትሮው ዝግጁነቱን የሚያጠናክርበት መሆኑን ገልጸዋል።

በየጊዜው የሚፈጠሩ ነገሮች ሰራዊቱን የሚያዳክሙ ሳይሆን ወደ ታላቅነት የሚወስዱት መሆኑን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በፈተናዎች ሁሉ ያለፈ ቁርጠኛ ሰራዊት መሆኑን ገልጸው፤ አሁንም ይበልጥ አይበገሬነቱን እያስመሰከረ መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም የጥንካሬ ተምሳሌት ሆኖ መቀጠሉን ገልጸው፤ በመከላከያ የተደረገው ሪፎርም ሰራዊቱን በውጤታማነት ወደፊት ማሸጋገሩን አንስተዋል።

እንዲሁም አመርቂ ድሎችን በማስመዝገብ ነገን የሚሻገር መሰረት መጣሉንና የሰራዊቱ ጥንካሬ የኢትዮጵያ ጥንካሬ መሆኑን ሚኒስትሯ አያይዘው ገልጸዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም