በኢትዮጵያ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ሽፋን እየሰፋ መምጣቱ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ሽፋን እየሰፋ መምጣቱ ተገለጸ
ቦንጋ ፤ ጥቅምት 14/2017 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎትን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በተካሄደው እንቅስቃሴ ሽፋኑ እየሰፋ መምጣቱን የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት አስታወቀ።
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የመክፈል አቅምን መሰረት ያደረገ የመዋጮ አሰባሰብ ማስፈጸሚያ ማኑዋል የማስተዋወቂያ መድረክ በቦንጋ ከተማ ዛሬ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ በመድረኩ ላይ እንዳስታወቁት ከ13 ዓመት በፊት በጥቂት ወረዳዎች የተጀመረው የህብረተሰብ ጤና መድህን አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ በ1 ሺህ 52 ወረዳዎች ተደራሽ ማድረግ ተችላል።
በዚህም እንደ አገር የአገልግሎት ሽፋን በማስፋት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።
በቀጣይም አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ለማድረስ የመክፈል አቅምን መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።
ይህም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መክፈል የሚችለውን ያህል በመክፈል የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚሆን አስረድተዋል።
ሁሉም ባለድርሻ አካላት የአሰራር ሥርዓቱን በቁርጠኝነት በመተግበር ለአገልግሎቱ ቀጣይነት የድርሻቸውን እንዲወጣ ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊና የህክምና አገልግሎት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ምትኩ ታመነ በበኩላቸው፤ የክልሉን ጤና መድህን አገልግሎት ሽፋን 55 በመቶ ማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ 300 ሺህ የሚጠጉ አባላት የህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ ለዚህም 44 ሚሊዮን ብር ለጤና ተቋማት ክፍያ መፈፀሙን ተናግረዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ 135 ሚሊዮን ብር ከአዲስና ነባር አባላት እድሳት በመሰብሰብ በተከፈተው አካውንት ገቢ መደረጉን የጠቆሙት አቶ ምትኩ፤ በበጀት ዓመቱ የአባላትን ቁጥር ከማሳደግ ባለፈ ቀጣይነቱን ማረጋገጥ ላይ አፅንኦት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
ለዚህም ዜጎች ባላቸው ገቢ መጠን እንዳቅማቸው ክፍያ የሚፈፅሙበት ስርዓት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም "በጤና ተቋማት የሚስተዋለውን የመድሀኒት አቅርቦትና የአገልግሎት ጥራት መጓደልን ለማሻሻል ይረዳል " ብለዋል።