የደቡባዊ ዓለም ሀገራት ለዓለም የአስተዳደር ስርዓት ለውጥ በጋራ መነሳት አለብን-አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡባዊ ዓለም ሀገራት ለዓለም የአስተዳደር ስርዓት ለውጥ በጋራ መነሳት አለብን-አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ
አዲስ አበባ፤ጥቅምት14/2017(ኢዜአ)፦የደቡባዊ ዓለም ሀገራት ለዓለም የአስተዳደር ስርዓት ለውጥ በጋራ መነሳት አለብን ሲሉ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ተናገሩ።
የብሪክስ 16ኛ ጉባኤ ሦስተኛ ቀን ውሎ በሩሲያ ካዛን እንደቀጠለ ነው።
በጉባኤው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፤ የደቡብ ደቡብ ትብብርና የብሪክስ ጥምረት መጠናከር ወሳኝ ነው ብለዋል።
በዓለም ላይ እያጋጠሙ ያሉ ቀውሶችን ለመፍታት የጋራ አቅምን ማሰባሰብ ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።
የደቡብ ደቡብ ትብብርን በማጠናከር በሀገራት የሚስተዋሉ ግጭቶችን ማርገብና ሰብዓዊ ቀውሶችን መፍታት እንደሚቻልም ጠቁመዋል።
የልማት ፋይናንስን በማጠናከር ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት መነሳት አለብን ብለዋል።
እያደጉ የሚገኙ ሀገራት የደቡብ ደቡብ ትብብርን በማጠናከር እንዲሁም የጋራ ዓላማና ራዕይ በማስቀመጥ ለተሻለ የዓለም አስተዳደር ስርዓት ግንባታ ሪፎርም መትጋት የግድ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የደቡባዊ ዓለም ሀገራት የዓለም አቀፍ አስተዳደር እና የፋይናንስ ተቋማት ሪፎርም ቀዳሚ ትኩረታቸው እንዲያደርጉም ኢትዮጵያ ጥሪ አቅርባለች።
ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ለሚደረገው ጥረት የዕዳ ጫናን መቀነስና የልማት ፋይናንስ ድጋፍን መጨመር ወሳኝ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ምስጋኑ፤ የበለጸጉ ሀገራት የዕዳ ሽግሽግ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
ለዚህም ዓለም አቀፋዊ የአስተዳደር ሪፎርም እውን እንዲሆን ድምጻችንን በአንድነት ልናሰማ ይገባል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ዘርፈ ብዙ ሪፎርም የሁላችንም ቀዳሚ የትብብር ትኩረት መሆን አለበት ብላ ታምናለች ብለዋል።
በመሆኑም ደቡባዊ ዓለም ሀገራት ለዓለም የአስተዳደር ስርዓት ለውጥ በጋራ መነሳት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።
የደቡባዊ ዓለም በተለይም አፍሪካ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ተገቢውን ውክልና እንድታገኝ እጅ ለእጅ መስራት እንደሚገባ በመጠቆም የውክልና ኮታ ማሻሻያ እንዲደረግም ጠይቀዋል።
ከዚህም ባለፈ ደቡባዊው ዓለም ተጨማሪ አዲስ የልማት ፋይናንስ ስርዓትን ለማምጣት መወሰንና ወደ ተግባር መግባት እንዳለበት ገልጸዋል።
በደቡባዊ ዓለም የሚገኙ ሀገራት ትብብር የታዳጊ ሀገራትን አቅም በማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለው በማንሳት የንግድ፣ የኢንቨስትመንት ፍሰት፣ የልማት ፋይናንስና ቱሪዝም ትብብርን ማሳደግ አለብን ብለዋል።
በአካባቢው በርካታ ህዝብ መኖሩ ሰፊ የገበያ አቅም ነው ያሉት አምባሳደር ምስጋኑ፣ የቴክኖሎጂና የእርስ በእርስ ትስስር በፍጥነት እያደገ መምጣቱም የደቡባዊ ዓለም የንግድ ልውውጥ ለዓለም ጥቅል ንግድ ዋና አንቀሳቃሽ እንዲሆን አስችሎታል ነው ያሉት።
በመሆኑም የንግድ ሚዛን ጉድለትን ለማስተካከልና አቅምን አሟጦ ለመቀጠም በትብብር መስራት ወሳኝ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ከቀረጥ ነጻን ማበረታታትና የኮታ ገደብን ማሻሻል የንግድ ልውውጥን ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸውም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በጋዛና ሊባኖስ ያለው ግጭትና ውጥረት መባባስ እንዲሁም በርካታ ንጹሃንን ለጉዳት መዳረጉ ያሳስባታል ሲሉ አንስተዋል።
ግጭቱና ውጥረቱ በመካከለኛው ምስራቅ እንዳይስፋፋ በአፋጣኝ ማርገብ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሁሉም ተፋላሚዎች አስቸኳይ የተኩስ አቁም በማድረግ ግጭቱን በሰላም ለመፍታት ውይይት እንዲጀምሩ ትጠይቃለች ብለዋል።
በማንኛውም ሁኔታ ንጹሃን እንዳይጎዱ ተገቢውን ጥበቃና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
ሁሉም የቀጣናው ወሳኝ ተፋላሚ ኃይላት ከግጭት አባባሽ ድርጊታቸው በመታቀብ ሰላማዊ አማራጭን እንዲከተሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ የደቡብ ለደቡብ ትብብር ዓለም አቀፋዊ ሰላምና ደህንነት ላይ የተጋረጡ ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብላ እንደምታምንም ገልጸዋል።
ድህነትን ለመቀነስ፣ልማትን ለማፋጠን እና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም ትብብሩ ወሳኝ እንደሆነም አብራርተዋል።
ብሪክስ በፍጥነት እያደጉ በሚገኙ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት በእኩልነት፣ በአንድነትና በመከባበር መርህ የማጠናከር ሚናውን እንዲወጣ ኢትዮጵያ አበክራ እንደምትሰራም አረጋግጠዋል።