በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የኤሌክትሪክ ሃይል የማያገኙ ቀበሌዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የመስመር ዝርጋታ በመከናወን ላይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የኤሌክትሪክ ሃይል የማያገኙ ቀበሌዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የመስመር ዝርጋታ በመከናወን ላይ ነው
ሰቆጣ፤ ጥቅምት 14/2017 (ኢዜአ)፡- በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ሶስት ወረዳዎች የኤሌክትሪክ ሃይል የማያገኙ ቀበሌዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የምሰሶ ተከላና የመስመር ዝርጋታ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
በአገልግሎቱ የአማራ ክልል ወልዲያ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃብታሙ እማኛው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኤሌክትሪክ ሃይል በማቅረብ የአገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑት ሰባት ቀበሌዎች ናቸው።
በዚህም የመካከለኛና አነስተኛ ሃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ተከላ ስራና የመስመር ዝርጋታ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሃይል አቅርቦቱ የሚመቻቸው በሰቆጣ፣ ፃግብጂና አበርገሌ ወራዎች በሚገኙ ፃና፣ወርቃዲኑ፣እጥቅኑ ፣ምቁን ፣አርሸርዋ፣ፃታ እና እክመፅርዋ ቀበሌዎች የሚኖሩ አንድ ሺህ 211 እማወራና አባዎራዎች ተጠቃሚ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
ተጠቃሚዎቹም የቆጣሪ ለማስገባት የሚያስችላቸውን ምዝገባ ማከናወናቸውን ጠቅሰው፤ ለሃይል አቅርቦቱም ከ165 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን አመልክተዋል።
በሶስቱ ወረዳዎች የሚገኙ ሰባት ቀበሌዎችን ከቀጣዩ ወር ጀምሮ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች በመከናወን ላ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የህብረተሰቡን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚነትን ለማስፋት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑ የተናገሩት አቶ ሃብታሙ፤ ህብረተሰቡም የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።
የፃግብጅ ወረዳ የአስተዳደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ወልደ ጊዮርጊስ ገብሩ ፤ በወረዳው የሚገኙ አራት ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ከሰኔ ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባም የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በተሟላ መንገድ ይፈታል ብለዋል።
በፃግብጅ ወረዳ የፃታ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል አቶ ቀናው ብርሃኑ በሰጡት አስተያየት፤ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ሲቸገሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
አሁን ፃታን ጨምሮ በአካባቢው ያሉ መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ስራ ተጠናቆ አገልግሎት ሲበቃ ችግራቸው ይፈታል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቱን ተደራጅተው እንደሚጠብቁም አስታውቀዋል።