ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ የ45 የሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመች

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 14/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ (Green Climate Fund) የ45 የሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ዛሬ ተፈራርማለች።

የአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ 40ኛ መደበኛ ስብስባውን በኮሪያ ሪፐብሊክ ሶንድጎ ከተማ አካሄዷል።

የፈንዱ ቦርድ በድርቅ በተጠቁ የኢትዮጵያ ክፍሎች የውሃ ዋስትናን ማረጋገጥ አላማ ያደረገ የ50 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ፕሮጀክት አጽድቋል።

ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ከሚውለው አጠቃላይ የ50 ሚሊዮን ዶላር በጀት ውስጥ 45 ሚሊዮን ዶላሩ በአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ የሚሸፈን ነው።

ቀሪውን አምስት ሚሊዮን ዶላር የኢትዮጵያ መንግስት እንደሚሸፍን ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ከአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ ለምታገኘው የ45 የሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ስምምነት ተፈራርማለች።

ስምምነቱን የተፈራረሙት በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ እና የአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ ዋና የኢንቨስመንት ኦፊሰር ሄንሪ ጎንዛሌዝ ናቸው።

ፕሮጀክቱ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ ስርዓት በመዘርጋት የውሃ ዋስትናን ማረጋገጥን አላማ ያደረገ መሆኑ ተመላክቷል።

ከ335 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ በሚያደርገው ፕሮጀክት አማካኝነት የሚዘረጋው የውሃ አጠቃቀም ስርዓት በዘላቂነት ለመጠጥ እና መስኖ የሚሆን ውሃ በዘላቂነት እንደሚስብ ተጠቁሟል።

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን ደህንነቱ የተጠበቀ ውሃ ተደራሽነት ዓለም አቀፍ ግብ ለማሳካት እና ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተጋላጭነት ባለባቸው አካባቢዎች የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚያስችል ተመላክቷል።


 

በተጨማሪም ድጋፉ ኢትዮጵያ የያዘቻቸውን የአየር ንብረት ለውጥ ግቦች ለማሳካት እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ እንዳለው በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ (Green Climate Fund) እ.አ.አ በ2010 የተቋቋመ ሲሆን ዋና መቀመጫውን በኮሪያ ሪፐብሊክ ሶንድጎ አድርጓል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነትን መሰረት አድርጎ የተቋቋመው ፈንድ በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም እና መከላከል ላይ ለሚያከናውኑት ስራ የፋይናንስ ድጋፍ ያደርጋል።

የአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ በዓለም ላይ ከሚገኙ የአየር ንብረት ለውጥ ከሚገኙ ፈንዶች መካከል ትልቁ እንደሆነ ይነገርለታል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም