ቀጥታ፡

በክልሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት እና አገልግሎትን ለማሻሻል በቅንጅት ይሰራል-አቶ እንዳሻው ጣሰው

ሆሳዕና፤ጥቅምት 14/2017 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኤሌክትሪክ ተደራሽነት እና አገልግሎትን ለማሻሻል በቅንጅት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።

በክልሉ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ያሉ ችግሮች በሚፈቱበት ሁኔታ በሆሳዕና ከተማ ምክክር ተካሄዷል።

በዚህ ወቅት አቶ እንዳሻው ጣሰው እንዳሉት የኤልክትሪክ መቆራረጥ፣ የኃይል አቅርቦትና ተደራሽነት ችግር በክልሉ በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ላይ እክል እየፈጠረ ነው።

ይህም አምራች ኢንዱስትሪዎችን እየፈተነ ሲሆን በኦን ላይን ገቢ አሰባሰብ፣ በሥራ እድል ፈጠራና ሌሎች ዘርፎች ላይ የሚጠበቀውን ያህል ውጤት እንዳይመዘገብ ተግዳሮት እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል።

በክልሉ ለህብረተሰቡ ፍትሃዊና ቀልጣፋ የኤሌክትሪክ አግልግሎትን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ በመስሪያ ቤቱ ሠራተኞች ዘንድ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደርና የብልሹ አሰራሮችን ማረም እንደሚገባም አመላክተዋል።

በመሆኑም እነዚህ ችግሮች እንዲፈቱና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ የክልሉ መንግስት ከአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በተለይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተዘረጉ መሰረተ ልማቶችን ደህንነት ለማስጠበቅ  ትኩረት መሰጠቱንም ጠቁመዋል።


 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው አገልግሎቱ ደንበኛ ተኮር የሆኑ አሰራሮችን በመዘርጋት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በማህበረሰቡ ዘንድ ለሚነሱ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል እቅድ ተዘጋጅቶ በመተግበር ላይ እንደሚገኝም ነው ያነሱት።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ ከተሞች ለረዥም ዘመናት ያገለገሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ማርጀትና ለብልሽት መዳረግ ከኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ጋር ለሚነሱ ችግሮች በምክንያትነት የሚጠቀስ ናቸው ብለዋል።

በክልሉ እነዚህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል እቅድ ተቋማቸው ማዘጋጀቱንም ነው የጠቀሱት።


 

የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ናትናኤል ሚሊዮን በክልሉ በሚገኙ አስር ከተሞች ውስጥ 144 ሼዶች ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

123 ፋብሪካዎች ሼዶቹን ተረክበው የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ በኃይል መቆራረጥ ምክንያት የሚጠበቅባቸውን ያህል ምርት በማምረት ላይ እንዳልሆኑ አስረድተዋል።

አሁን ላይም በክልሉ መንግስት 100 አዳዲስ ሼዶች ተገንብተው መጠናቀቃቸውንና በኤሌክትሪክ አቅርቦት ፈጣን አገልግሎት ባለማግኘታቸው ሼዶቹን ወደ ስራ ለማስገባት አልተቻለም ብለዋል።

የኤሌክትሪክ አገልግሎት በዘርፉ ለሚስተዋሉ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ተገቢውን ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም