በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት በፈጣን እድገትና የላቀ አገልገሎት ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት በፈጣን እድገትና የላቀ አገልገሎት ቀጥሏል
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 14/2017 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎትና ዲጅታላይዜሽን በፈጣን እድገትና የላቀ አገልገሎት መቀጠሉን የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይዎት ታምሩ ገለጹ፡፡
ኢትዮ-ቴሌኮም እና ጂ.ኤስ.ኤም.ኤ በጋራ በመሆን ባለፉት አመታት በመላ አገሪቷ የተከናወኑ የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ስራዎችን ተዘዋውረው በመመልከት መረጃዎችን ሰብስበዋል፡፡
በመስክ ምልከታ የሰበሰቧቸውን መረጃዎችም በዛሬው እለት ይፋ አድርገዋል፡፡
የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩንና የጂ.ኤስ.ኤም.ኤ ግሎባል ሬጉላቶሪ ኦፊሰር ጆን ጊዩስቲ ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በኢትዮጵያ የቴሌኮም ማሻሻያ እና የሞባይል ቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በአምራች ዘርፍ፣ በሕዝብ አገልግሎትና ሌሎችም ዘርፎች ፈጣን እድገት መታየቱ በሪፖርቱ ተመላከቷል።
እኤአ በ2023 በዘርፉ 700 ቢሊዮን ብር ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ የታክስ ገቢ እንዲገኝ ማስቻሉ ተገልጿል፡፡
የሞባይል ኢንተርኔት ግንኙነትም ወደ 65 በመቶ ማደጉንና የ4ጂ ሽፋንም በአራት እጥፍ መጨመሩ ተነስቷል።
ከዚህም በመነሳት የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ እኤአ በ2028 ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት 1 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ተገምቷል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ የመስክ ምልከታው ለ4 ወራት የተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም የማሻሻያ እርምጃዎች እና ያመጡ ለውጦች መቃኘታቸውን ገልጸዋል።
በ2018 የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር 37 ሚሊዮን እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ 79 ሚሊዮን መድረሱን ጠቁመዋል።
የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችም ከ16 ሚሊዮን ወደ 46 ሚሊዮን ማደጉን አንስተው አጠቃላይ የዲጅታል አገልግሎትም ከፍተኛ እድገት የተመዘገበበት ሆኗል ብለዋል።
የጂ.ኤስ.ኤም.ኤ ግሎባል ሬጉላቶሪ ኦፊሰር ጆን ጊዩስቲ፤ ኢትዮጵያ በዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ እያከናወነች ያለው ተግባር ለሌሎችም የአፍሪካ አገራት በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሞባይል ኔትዎርክ ኦፕሬተሮችን የሚወክለው ጂ.ኤስ.ኤም.ኤ፤ የሞባይል ኦፕሬተሮች እና መለስተኛ ኦፕሬተሮችን ጨምሮ 26 የቦርድ አባላት ያሉት ዓለም አቀፍ ተቋም ነው፡፡