አገራት ሁሉንም ተጠቃሚ ያደረገ ፍትሃዊ ዓለም ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት በጋራ ሊቆሙ ይገባል

አዲስ አበባ፣ጥቅምት 14/2017( ኢዜአ)፦የመንግሥታቱ ድርጅት አባል አገራት ሁሉንም ተጠቃሚ ያደረገ ፍትሃዊ ዓለም ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥሪ አቀረበ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀን የድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተከብሯል።

በመርኃ-ግብሩ ላይ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ መልዕክት የድርጅቱ ረዳት ዋና ፀሐፊ እና የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ዶክተር ራሚዝ አላክባሮቭ አስተላልፈዋል። 

ዋና ፀሐፊው በመልዕክታቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ከተመሠረተ አንስቶ ላለፉት 79 ዓመታት ለዓለም አቀፍ ችግሮች መፍትሔ በማበጀት የላቀ ሚናውን መወጣቱን አስታውሰዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር፣ የዓለም አቀፍ ሕግ እሴቶችና መርሆዎች በእያንዳንዱ ሰው ክብር እንዲሁም ሰብአዊ መብቶች ውስጥ ስለመሆኑ አንስተው፤ በቀጣይም ለዓለም ዘላቂ ሰላምና ሰብአዊ መብት መከበር ሁለገብ መፍትሔ ያስፈልጋል ብለዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት አባል አገራት ሁሉንም ተጠቃሚ ያደረገ ፍትሃዊ ዓለም ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት በጋራ እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል።


 

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር የትምህርት ጉዳዮች አማካሪ ጋኦጋካላ ሌመንያኔ፤ የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጋርነት ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱን ገልፀዋል።

በተለይም በሰላምና ደህንነት፣ በዘላቂ ልማት እና ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ እና ሌሎችም ጠንካራ ትብብር መፈጠሩን አንስተዋል።


 

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዳይሬክተር ጄኔራል ሰሙንጉስ ገብረሕይወት፤ ኢትዮጵያ በዓለም የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ትልቅ አስተዋጽዖ ማበርከቷንና አሁንም መቀጠሏን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በሚሊየን የሚቆጠሩ ስደተኞችን በመቀበል እያስተናገደች ስለመሆኗ አንስተው በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧም ይበልጥ ተቀራርባ ለመስራት የሚያግዛት መሆኑን ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀን ድርጅቱ እ.አ.አ 1971 ባሳለፈው የውሳኔ ሀሳብ ቁጥር 2782 መሠረት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በየዓመቱ ጥቅምት 24 ይከበራል።

እለቱ እ.አ.አ 1945 የተቋቋመውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምሥረታ በማሰብ የሚከበር ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ አገራትና ተቋማት የመንግሥታቱን ድርጅት እሴቶች እንዲሁም ዓላማዎች በሚያስተዋውቁ ዝግጅቶች እና ተግባራት ይከበራል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም