ህብረተሰቡን በማሳተፍ የመዲናዋን ሰላምና ፀጥታ ዘላቂና አስተማማኝ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል -የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡን በማሳተፍ የመዲናዋን ሰላምና ፀጥታ ዘላቂና አስተማማኝ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል -የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2017(ኢዜአ)፦ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የመዲናዋን ሰላምና ፀጥታ ዘላቂና አስተማማኝ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ገለፀ።
የአዲስ አበባ ከተማ የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የ 2017 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ አመት የሰላምና ፀጥታ አፈፃፀሙን በየደረጃው የሚገኙ የህዝብ አደረጃጀቶች በተገኙበት ገምግሟል።
የመዲናዋ የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ሃላፊ ሚዴቅሳ ከበደ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በመዲናዋ በመጀመሪያው ሩብ አመት የህዝብ አደረጃጀቶችን በማጠናከርና በስፋት በማሳተፍ ሰላምን በዘላቂነት ማስጠበቅ ተችሏል።
ህዝቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ ወንጀልን ቀድሞ በመከላከልና የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ሰፊ ስራ መሰራቱን አስታውቀዋል፡፡
በመዲናዋ 11 ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች የንድፈ ሀሳብና የመስክ ስልጠና በመስጠት ወደ ሰላም ሰራዊት ገብተው የሰላምና ፀጥታ ስራዎችን እንዲሰሩ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
የመዲናዋን ሰላምና ፀጥታ ዘላቂና አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ማስጠበቅ መቻሉን በመጥቀስ የኮሪደርና ሌሎች የልማት ስራዎች እንዲፋጠኑ የማድረግ ተግባር መከናወኑን ተናግረዋል።
በበጀት አመቱ የመጀመሪያዎቹ ሶሰት ወራት በመዲናዋ የተከበሩ የአደባባይ በዓላት በድምቀት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም የአፍሪካ ከተሞች ስብሰባ በሰላም እንዲካሄድ መደረጉን አስታውሰዋል።
በበጀት አመቱ 60 ሺህ የሚሆኑ የሰላም ሰራዊት አባላትን በንድፈ ሀሳብና በመስክ ስልጠና በማብቃት ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይ የህዝቡን ተሳትፎና ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የመዲናዋን ሰላምና ፀጥታ ዘላቂና አስተማማኝ በሆነ መልኩ የማፅናት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የመዲናዋን ሰላም በመጠበቅና በልማት ስራዎች በመሳተፍ የተጣለባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።
የአካባቢያችንን ሰላም በጽናት በመጠበቅ የመዲናዋ ልማት እንዲፋጠን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
የመዲናዋን ሰላም በሁለንተናዊ መልኩ ለማፅናት በየደረጃው ከሚገኙ አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር መስራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።