የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓትን በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው- ባለስልጣኑ

ዲላ ፤ ጥቅምት 14/ 2017(ኢዜአ)፡- በፌደራል ተቋማት ተግባራዊ የተደረገውን የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በዲላና አካባቢው ላሉ የንግዱ ማህበረሰብ በኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ አሰራርና ምዝገባ ላይ የውይይትና የስልጠና መድረክ እያካሄደ ነው።


 

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወልደአብ ደምሴ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ ባለፈው ዓመት የኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ ስርዓትን በሁሉም የፌደራል የመንግስት ተቋማት ተግባራዊ በማድረግ የግዥ ግልጸኝነትንና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ተችሏል።

በዚህም በዓመቱ ከ325 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው 22ሺህ 223 የመንግስት ግዥዎችን በኤሌክትሮንክስ ሥርዓት ለመፈፀም መቻሉን አስረድተዋል። 

ይህም ቀልጣፍ የመንግስት ግዥ ሥርዓትን ለመተግበር ከማስቻሉ ባለፈ በጨረታ ሰነድ ሽያጭ፣ በግምገማና ውጤት ይስተዋሉ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ማስቀረቱን ገልጸዋል።

እንዲሁም የሃብትና የጊዜ ብክነትን በማስቀረት ግልጽነትና ተደራሽነትን ማረጋገጥ መቻሉን ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ያስታወቁት።

ይህንኑ ተሞክሮ ወደ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በማውረድ የመንግስት ግዥና ሽያጭ አገልግሎትን ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ይሁንና ለውጥን ለመቀበል ዝግጁ አለመሆን እንዲሁም የአመለካከት ችግሮች በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎች ስለመሆናቸው ነው የገለጹት።

ተከታታይ ስልጠና በመስጠትና የውይይት መድረኮችን በማካሄድ ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ መድረኩም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይ መድረኩ የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት ምዝገባን ያካተተ በመሆኑ በዲላና አካባቢው ያለው የንግዱ ማህበረሰብ እድሉን በመጠቀም ተወዳዳሪነቱን እንዲያሰፋ አስገንዝበዋል።

የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት ግልጽ የሆነ የግዥ ስርዓት መፍጠሩን ያነሱት ደግሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤልያስ አለሙ ናቸው።


 

በተለይ አቅራቢዎች በበይነ መረብ ካሉበት ሆነው ከዩኒቨርሲው የግዥ ፍላጎት አንጻር ምርትና አገልግሎት በማቅረብ በትስስር ለመስራት ያስቻለና አሰራሩን ያቃለለ ነው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ያሉትን የግንዛቤ ችግሮች ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይ የንግዱ ማህበረሰብ ምዝገባ በማድረግ ከአካባቢው ባለፈ በሀገር አቅፍ የግዥ ጨረታዎች ላይ መሳተፍ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የባለስልጣኑና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም የዲላና አካባቢው የንግዱ ማህበረሰብ አባላት መሳተፋቸው ታውቋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም